(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 5/2011)የሰኔ 16ቱን የቦምብ ጥቃት አስተባብረዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩት የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ባልደረባ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፖሊስ የሚያደርገውን ምርመራ እንዲያጠናቅቅ ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጠ ፡፡
ፖሊስ ችሎቱ በፈቀደለት 10 ቀናት የሰው ምስክር መቀበሉን ብሎም ከመስሪያ ቤታቸው የተገኘው ቦምብ ለምርመራ መወሰዱንና ሌሎች ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሷል፡፡
ፖሊስ የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌን በተመለከተ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎትን ለተጨማሪ የምርመራ ስራ 10 ቀናት እንዲፈቀደለት ጠይቋል፡፡
የሰኔ 16ቱን የቦምብ ጥቃት አስተባብረዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በቡኩላቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ 4 ወራት መቆጠሩንና ፖሊስ የሚጠይቃቸው የግዜ ቀጠሮዎች ተገቢነት የላቸውም በማለት ቅሬታችውን አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ቦምብ ከቤቴ ሳይገኝ ከቤቱ ተገኝቷል እያሉ በመዘገባቸውም ሰብአዊ መብቴ ተነክቶብኛል ብለዋል።
እናም ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ በማለት ፍርድቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥልኝ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ ታዲያ ከእውነታው ውጭ የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ሰለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ትዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።
የጊዜ ቀጠሮውን በተመለከተ ደግሞ ፖሊስ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ የመጨረሻ ቀጠሮ በማለት 7 ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለጥቅምት 12 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment