(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011) ግሎባል አልያንስ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ለተፈናቀሉ ከ70ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የገንዘብ ማሰባብሰብ ዘመቻ በይፋ መክፈቱን አስታወቀ።
አለም ዓቀፍ መብት ለኢትዮጵያውያን ግሎባል አሊያንስ በጎ ፈንድ ሚ አማካኝነት ለከፈተው ዘመቻ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ወጣቶች ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመነጋገር ለቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቃዮች የተለያዩ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገለጿል።
የማይበላሹ ምግቦች የንጽህና ቁሶች፡ ብርድልብስና አልባሳት መስጠት ለሚችሉ ኢትዮጵያውያን በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ቅጥር ግቢ በመምጣት እንዲሰጡ ጥሪ አድርገዋል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ ብሄር ተኮር ጥቃት ይቁም በሚል በግሎባል አሊያንስ ዛሬ የተከፈተው የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ለጊዜው ግቡን 25ሺህ የአሜሪካን ዶላር አድጓል።
ለኢትዮጵያውያን መብት በመቆም በችግራቸው ጊዜ እየደረሰ በመደገፍ ላይ የሚገኘው ግሎባል አልያንስ ትኩረቱን ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ አድርጓል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ጥቃት የደረሰባቸውና በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ዜጎች ወደ አጎራባች አከባቢዎች መሸሻቸው የተገለጸ ሲሆን ቁጥራቸው 70 ሺህ መድረሱም ታውቋል።
በምስራቅ ወለጋ በተለያዩ አከባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በአደጋ ውስጥ መሆናቸውን የገለጸው ግሎባል አልያንስ፥ የምግብ አልባሳትና የመድሃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ከፍተኛ ስብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ጠቅሷል።
መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች፣ በህክምና ላይ የነበሩ ታማሚዎች፣ አቅመደካማ የሆኑ አዛውንቶችና ህጻናት በአብዛኞው የሚገኙበት ተፈናቃይ ማህበረሰብ አስቸኳይ ድጋፍ ማግኘት እንደሚገባው ግሎባል አሊያንስ አስታውቋል።
የግሎባል አሊያንስ ዳይሬክተር አርቲስት አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙት ዜጎቻችን ኢትዮጵያውያን የተለመደውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናችን ቁሙ ሲል ጥሪ አድርጓል።
በዛሬው ዕለት ይፋ በተደረገውና ለቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚወለውን የጎፈንድ ሚ ዘመቻ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ህዝቡ ድጋፉን እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በተያያዘ ዜናም የአዲስ አበባ ወጣቶች ከቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለው በምስራቅ ወለጋ ለተጠለለ ከ70ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የቁሳቁስ ስጦታ ከህብረተሰቡ መጠየቁ ተገልጿል።
በአክቲቪስት ያሬድ ሹመቴ አስተባባሪነት ድጋፍ ለመሰብሰብ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ወጣቶች ጉዳዩ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር መነጋገራቸውም ታውቋል።
በመጪው መስከረም 28 እና 29 ማለትም ሰኞና ማክሰኞ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ቅጥር ግቢ በተዘጋጀ የመረከቢያ ቦታ በመምጣት የማይበላሹ ምግቦች፣ አልባሳት፣ የንጽህና ቁሳቁሶችና ሌሎች በዓይነት የሚሰጡ ድጋፎችን እንዲያደርግ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ጥሪ አቅርበዋል።
ወጣቶቹ ከህዝቡ ያገኙትን የተለያዩ ቁሳቁሶችና ምግብ ወዲያውኑ ለተፈናቃዮቹ እንዲደርስ ለኦሮሚያ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ እንደሚያስረክቡም ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment