Monday, October 8, 2018

በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቤት መስሪያ ብድር ሊሰጥ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 28/2011)የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቤት መስሪያ ብድር ለመስጠት መወሰኑን ገለጹ።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊኒ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደምበኞቹን ለማገልገልና እራሱንም ለማሳደግ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላ ሃገሪቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅርንጫፍ ባንኮች ያሉት ግዙፍ የገንዘብ ተቋም ነው።
የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከ3 መቶ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ነው የሚነገረው። በሃገሪቱ ካለው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 67 በመቶው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገኛል።
በመላ ኢትዮጵያ ከተሰጡ ብድሮች ደግሞ ንግድ ባንኩ 53 በመቶውን ይሸፍናል።
እናም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የጀመሩትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት በማድረግ ለዲያስፖራው የቤት መስሪያ ብድር አመቻቻለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና ሰሞኑን ከዲያስፖራው አባላት ጋር ባካሄዱት ውይይት ባንኩ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለቤት መስሪያ የሚሆን ብድር ይመቻችላቸዋል ብለዋል።

ባንኩ ለዲያስፖራው ብድር ለማቅረብ የወሰነው በኢትዮጵያ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እየተወሰደ ካለው እርምጃ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራል።
በቅርቡም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ሲያስቀምጡ እስከ 50 ሺህ ዶላር ብቻ የነበረውን ገደብ አንስቷል።
እንደ ባንኩ ገለጻ ማንኛውም ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈለገውን መጠን ዶላር ዩሮና የመሳሰሉትን የውጭ ምንዛሪ ሊያስቀምጥ ይችላል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዲያስፖራው የቤት መስሪያ ብድር አመቻቻለሁ ቢልም የብድር አሰጣጡና የሚያስፈልገው መስፈርት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።

No comments:

Post a Comment