Wednesday, October 17, 2018

ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአርጎባ ብሄር ተወላጆች ከተጠለሉበት ትምህርት ቤት ተባረሩ። ለዜጎች መፈናቀል የወረዳ መስተዳሮች እጅ አለበት ተባለ።

( ኢሳት ዜና ጥቅምት 07 ቀን 2011 ዓ/ም ) ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ቦሌ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች በማንነት ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ቁጥራቸው ከ146 በላይ የሚሆኑ የአርጎባ ብሔር ተወላጆች አስታዋሽ አጥተን ለችግር ተዳርገናል አሉ። እስካሁንም በመንግስት በኩል በቂ ዕርዳታ እንዳልተደረገላቸው ጉዳተኞቹ ይናገራሉ። ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊ መጠለያነት ተጠግተው ይኖሩበት ከነበረው የመልካ ጅሎ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ እንዲወጡም ተደርገው ቀይ መስቀል በሰጣቸው ጊዜያዊ መጠለያ ድንኳን ውስጥ ተጠልለዋል። ቀይ መስቀል ብርድ ልብስ፣ ውሃ መጠጫ እና አንድ ከረጭት ዱቄት ብቻ የረዳቸው ሲሆን የወረዳው መስተዳድር ለአንድ ቤተሰብ በነፍስ ወከፍ አንድ ሽህ ብር ብቻ ከመርዳት ውጪ ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱም ሆነ መልሶ ለማቋቋም ያደረገላቸው እገዛ የለም። ቤተሰቦቻቸው ከሚያደርጉላቸው እገዛ በተጨማሪ የአርጎባ ህዝቦች ድርጅት የ100 ሺህ ብር እርዳታ የለገሰ ሲሆን፤ የምንጃር ወረዳ ወጣቶች በበኩላቸው ከጎናቸው በመቆም አስፈላጊውን እገዛ አድርገውላቸዋል። መንግስት መጠለያ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል ቢገባላቸውም ማረፊያ መጠለያን ጨምሮ ከመኖሪያቸው ባዶ እጃቸውን በመውጣታቸው የአልባሳት፣ የቁሳቁስ እና ምግም አላገኙም። በተለይም ሕጻናት ልጆች ያሏቸው ወላጆች ለተጨማሪ ጉዳቶች ተጋላጭ ሆነዋል። የሚመለከተው የመንግስት አካል ለችግራቸው በአፋጣኝ እልባት እንዲሰጣቸው ተማጽኖ አሰምተዋል። በአርሲ ቦሌ ለጠፈጠረው ችግሮች በአገር ሽማግሌዎች በኩል የማስታረቅ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በምስራቅ ሸዋ በኩል ግን እስካሁን አልተደረገም። ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ሥጋት
ስላለባቸውና ዋስትና የሚሰጣቸው ባለመኖሩ ለመመለስ ፈቃደኞች አይደሉም። ሕዝብ እንዳይጋጭ የክልሎቹ መስተዳደሮች ኃላፊነት ቢኖርባቸውም ግጭቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ የወረዳዎች አስተዳዳሪዎች መኖራቸውንና አንዳንድ ግጭቶች ሰው ሰራሽ ናቸው። የተፈናቀሉ የአርጎባ ብሄር ተወላጆች ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘታቸውንና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል የአዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ መሀመድ ሙሳ አስታውቀዋል። ግጭቶች እንዲፈጠሩ ያደረጉ የወረዳ መስተዳደር ካቢኔዎችን በማንሳት አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆኑን አሁንም በቂ ባለመሆናቸው በመሃል ላይ የአርጎባ ህዝብ መከራውን እየጋተ ነው። በሁለቱም ክልል በኩል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መሰራት፤ ከተፈጠሩ በኋላም መፍትሔ ለመስጠት ሥር ነቀል መፍትሔ ሊወሰድ ይገባል። ተፈናቃዮቹ ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘታቸውንና በሚቀጥሉት አስራ አምስት ቀናት ውስጥ በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አቶ መሀመድ ሙሳ አክለው ገልጸዋል። በምንጃር ወረዳ የመልካ ጅሎ መስተዳድርና ኃላፊን ለማነጋገር ያደረግናቸው ሙከራዎች አልተሳኩም። በመልካ ጅሎ የአሞራ ቤት ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሚልዮን ደርቤ ስልክ ካነሱ በኋላ ስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

No comments:

Post a Comment