Thursday, October 18, 2018

ለውጡን ለማደናቀፍ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ቤተመንግስት ተልከዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 8/2011) የታጠቁ ወታደሮችን ወደ ቤተመንግስት የላኩት አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
በወቅቱ ለድርጊቱ የጥንቃቄ ምላሽ ባይሰጥ ኖሮ ሃገሪቱን ወደ ቀውስ የሚከታት ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
ሆኖም ሁሉም ወደ ቤተመንግስት የተንቀሳቀሱት ወታደሮች ይህንን ግንዛቤ ጨብጠው ነበር ለማለት እንደሚያስቸግርም አመልክተዋል።
መስከረም 30 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት ቁጥራቸው 250 የሚሆን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከነትጥቃቸው ወደ ቤተመንግስት ያደረጉት ጉዞ አብይ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በወቅቱ ከሰራዊቱ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት የሰራዊቱ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አግባብ እንደነበር በመግለጽ ጥያቄውን ያቀረቡበት መንገድ ግን ሕገ ወጥ ነው ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።
የሰራዊቱ አባላት ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሰአረ መኮንንና ከሌሎች የሰራዊቱ አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ድርጊቱን ከበስተጀርባ የመሩና ያቀነባበሩ የሰራዊቱ አዛዦች መታሰራቸውን ጄኔራል ሰአረ መኮንን በሳምንቱ መጨረሻ አስታውቀዋል።
ከታሰሩት የሰራዊቱ አዛዦች ጀርባ ግለሰብም ይሁን ቡድን ካለ ምርመራ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ዛሬ ፓርላማ ውስጥ አብሰጡት ማብራሪያም ሰራዊቱ ወደ ቤተመንግስት የተንቀሳቀሰው ሐገራዊውን ለውጥ ለማደናቀፍ እንደነበር አመልክተዋል።
በእለቱ በጥንቃቄ ርምጃ ባይወሰድ ኖሮ ሐገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትገባ እንደነበርም አመልክተዋል።
ወታደሮቹ የሴራውን አቀነባባሪዎች አሳልፈው መስጠት መጀመራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወቅቱ ሁኔታውን በጥንቃቄና በጥበብ መያዙ ሃገርን ለማትረፍ ወሳኝ ርምጃ ነበር ብለዋል።
በወቅቱ በመዝናናት ስሜት መግለጫ የሰጡት ሕዝብ ለአጸፋ ከተለያየ አቅጣጫ እንቅስቃሴ በማድረጉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment