(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 6/2011)በጦላይ ወታደራዊ ካምፕ በስቃይ ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲፈቱ የተከፈተውን ዘመቻ ተከትሎ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ እንደሚፈቱ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደግፌ በዲ ለቢቢሲ አማርኛው እንደገለጹት ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይለቀቃሉ።
ኮሚሽነሩ ወጣቶቹ የታሰሩት በጎዳና ላይ ንብረት ሲያወድሙና ሁከት ሲፈጥሩ ነው ብለዋል።
ከአንድ ወር በላይ ሆናቸው። ክስ አልተመሰረተባቸውም። ፍርድ ቤትም አልቀረቡም። በጅምላ ታፈሰው፡ በየክፍለከተማው ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት ቆይተው፡ በሰንዳፋ እንዲሰባሰቡ ከተደረጉ በኋላ ወዶ ጦላይ ተወሰዱ።
ጦላይ የወታደራዊ ካምፕ ሲሆን ለጤና ጠንቅ የሆነ አስቸጋሪ አከባቢ ነው። የህወሀት አገዛዝ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ የፖለቲካ ውጥረቶች ወጣቶችን ለመቅጣት ከሚጠቀምባቸው ቦታዎች ጦላይ ዋናው እንደሆነ ይነገራል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በጅምላ ታፍሰው ወደ ጦላይ የተወሰዱትን ከ1ሺህ በላይ ወጣቶችን በተመለከተ የመንግስት ሃላፊዎች እርስ በእርሱ የሚጋጩ መረጃዎችን በመስጠት ቆይተዋል።
ቁማርና ሺሻ ቤቶች ላይ በተደረገ የፖሊስ ወረራ ወጣቶቹ እንደታሰሩ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
በኋላ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አህመዲን ሸዴ ወጣቶቹ የታሰሩት ለኦነግ መሪ አቀባበል ለማድረግ ከተዘጋጀው ፕሮግራም ጋር በተያያዘ መሆኑን ገለጹ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል ደግሞ የመንግስትን ታጣቂዎች መሳሪያ ሊነጥቁ የነበሩትን ነው የያዝነው ብለው ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ህገመንግስቱንና የወንጀለኛ መቅጫ ህጎቹን በጣሰ ሁኔታ፡ ክስ ያልተመሰረተባቸውን ወጣቶች አፍሶ ለህይወት አደገኛ በሆነ ቦታ እንዲቀመጡ ማድረግ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ለዶክተር አብይ አስተዳደር ድጋፉን ላሳየው የአዲስ አበባ ህዝብ እንዲህ ዓይነት ቅጣት አኡገባውም የሚሉ ድምጾች በርክተው ነው የሰነበቱት።
ከትላንት ሰኞ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የበይነ መረብ ዘመቻ በግፍ የትሰሩትና በጦላይ በስቃይ ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲፈቱ የሚጠይቅ እንቅስቃሴ በመንግስት አከባቢ ጫና መፍጠሩን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ዘመቻው በሁለተኛ ቀኑ ላይ እያለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጦላይ የሚገኙት ወጣቶች በዚህ ሳምንት እንደሚፈቱ ገለጹ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩም ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ይህንኑ በማረጋገጥ ወጣቶቹ ሀሙስ ዕለት ይፈታሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄነራል ደግፌ በዲ ለቢቢሲ አማርኛ እንድገለጹት ወጣቶቹ በጎዳና ላይ ንብረት ሲያወድሙና ሁከት ሲፈጥሩ የተያዙ ናቸው፡፡
የፈፀሙት ተግባር በህግ የሚያስጠይቃቸው ቢሆንም መታነፅ እንዳለባቸው በማመን ስልጠና ተሰጥቷቸው ይለቀቃሉ በማለት ገልጸዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው በጦላይ የታሰረ የአንድ ወጣት እናት ልጃቸው ችግሩ ተፈጠረ በተባለበት ዕለት ከቤት አልወጣም፡ እንደዛ ዓይነት ወንጀልም አልፈጸመም ይላሉ።
No comments:
Post a Comment