(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 8/2011) በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊየን መጠጋቱን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ።
ከጥር እስከ ነሐሴ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከ36 ሺ በላይ መሆኑን የገለጸው ይህው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር መከፈቱን ተከትሎም የስደተኞቹ ቁጥር መጨመሩን አመልክቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ ነሐሴ 31/2018 በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር 905ሺ 831 መድረሱን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የደቡብ ሱዳን ተወላጆች መሆናቸውን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች 422ሺ 240 ሲሆኑ በብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት በቁጥር 257ሺ 283 የሚሆኑት ሶማሊያውያን ናቸው።
173ሺ ኤርትራዊያን ሲገኙ 44ሺ 620 ሱዳናውያን እንዲሁም 1ሺ 891 የመናውያንም በኢትዮጵያ ተጠልለዋል።
5ሺ 918 ስደተኞች ደግሞ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መሆናቸው ተመልክቷል።
የስደተኛው ቁጥር በመጨመር ላይ መሆኑን የገለጸው የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከጥር እስከ ነሃሴ ብቻ ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 36ሺ 185 እንደሆነ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ አዲስ አመት የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር በዛላ አምባሳና በራማ መከፈቱን ተከትሎ 6ሺ 779 ኤርትራውያን ስደተኞች ኢትዮጵያ መግባታቸውንም አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስደተኞችን ለማስተናገድ የ327 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጥሪ ማቅረቡን የገለጸ ሲሆን የተገኘው ገንዘብ ከተጠየቀው 2 በመቶ ወይንም 68 ነጥብ 3 ሚሊየን ብቻ እንደሆነም ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment