(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 22/2011) በአፋር፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የለውጥ እንቅስቃሴን የሚያዳፍኑ አመራሮች ህዝቡን እያሰቃዩ ናቸው ተባለ።
የአፋራ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅትና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዛሬ በአዲስ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል።በሶስቱ ክልሎች ያሉት አመራሮች ለውጡን እያደናቀፉት በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የአፋር ወጣቶች በህወሃት የሚንቀሳቀሰውን የጨው ምርት ንግድ ማገታቸውን የደረሰን መረጃ ያመልክታል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቲና የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሶስት ክልሎች የቀጠለውን የጭቆና አስተዳደር መንግስት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በሌላው የኢትዮጵያ አከባቢዎች እንደታየው የለውጥ ሂደት በአፋር ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ሊታይ አልቻለም ያሉት የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች የህወሀት ዘመን አሰራር አሁንም በክልሎቹ ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል።
የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ ለኢሳት እንደገለጹት እሳቸውን ጨምሮ የአፋር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ለአንድ ወር ያህል ወደ አፋር እንዳይሄዱና በአዲስ አበባ እንዲቆዩ ተደርገዋል።
የአፋርን ክልል የሚያስተዳድረው ፓርቲና አመራሮቹ በህወሀት ሰዎች የተከበቡና የጥቅም ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የነበረውን ለማስቀጠል እንጂ ለውጡን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ አፋር እንዳንሄድ እንቅፋት ሆነው ቆየተዋል ብለዋል።
በፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ገብነት ወደአፋር የሄደው የልዑካን ቡድን በክልሉ አመራሮች ወከባዎችና መሰናክሎች እንደተፈጸመበት የገለጹት አቶ ገአስ ደጋፊዎቻችን እንዳናገኝ ተደርገናል ሲሉም ገልጸዋል።
በአፋር ቆያታቸው በክልሉ አሁንም የህወሀት ዘመን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቀጠሉን መረዳታቸውን ጠቅሰው ህዝቡ ለውጡ እኛ አልደረሰም የሚል ቅሬታ እያሰማ ነው ብለዋል።
በአፋር ለውጡን በመደገፍ ሀሳቡን የሚገልጽ ከተገኘ በክልሉ አመራሮች ከድብደባ ጀምሮ እስራት ይፈጸምበታል ያሉት አቶ ገአስ አህመድ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ በአፋር የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ ሊወጣ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ያለውን ሁኔታ የገለጹት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ የለውጡ ንፋስ ያልደረሰበት ክልል ሲሉ ነው የጋምቤላን ወቅታዊ ሁኔታ የገለጹት።
አቶ ኦባንግ በቅርቡ ወደጋምቤላ ባመሩበት ወቅት የክልሉ አመራሮች ጉብኝታቸውን ለማደናቀፍ የፈጽሟቸውን ተጋባራት ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናት አሁንም ህዝቡን በቆየው የጭቆናና አስተዳዳአር እንዲቆይ እያደረጉት መሆናቸው የገለጹት አቶ ኦባንግ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ቁጣ ላይ ነው ብለዋል።
በአፋር ጋምቤላ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ የከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በተሰጠው መግለጫ የተገለጸው።
በአመራር ላይ ያሉት ሹማምንት ለውጡን አለመደገፋቸው መረን የለቀቀው ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት፡ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሥራአጥነት፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ ሰላማዊ ሰልፍ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ መከልከሉን በመግለጫው በዝርዝር ተብራርቷል።
መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ካልሰጠ በሶስቱ ክልሎች የማያባራ ተቃውሞ ሊፈነዳ ይችላል ብለዋል።
በሌላ በኩል የአፋርን ወጣቶች በማፈናቀል የጨው ምርት የተቆጣጠሩት አንድ የህወሀት ባለሀብት ላይ ህዝቡ ተቃውሞ ማሰማቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ህዝቡ የጨው ምርቱን እንዳይንቀሳቀስ በማገት ተቃውሞውን እየገለጸ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment