Friday, July 28, 2017

የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር የአብርሃ ደስታ የክስ መዝገብ ተዘጋ 

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 21/2009)የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ 8 ጊዜ በፖሊስ ተገደው ችሎት ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መዝጋቱን ገልጸ። አቃቢ ህግም ሆነ ፖሊስ በውሳኔው በመስማማት ዝምታን መርጠዋል የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ ቢቀርብላቸውም እሳቸው ግን መምጣት አልቻሉም። ስለዚህም ፍርድ ቤቱ መዝገባቸውን መዝጋቱን አስታውቋል። አቶ አብርሃ ደስታ ፍርድ ቤቱ ሲጠራቸውም ሆነ ከወር በሗላ መዝገቡን ሲዘጋ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀሌ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ ናቸው ። በሐምሌ ወር 2006 ከአቶ ሃብታሙ አያሌው ፣አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር በሽብር ተከ
ሰው ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ተወስደው የታሰሩት አቶ አብርሃ ደስታ፣ከአመት በኋላ ከሌሎች ጋር ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቷቸዋል። አቃቢ ህግ በአቶ ሺበሺና በአቶ አብርሃ ደስታ ላይ ይግባኝ በማቅረቡ አቶ ዳንኤል ሲታሰር አቶ አብርሃ በፍርድ ቤት ጥሪ ቢቀርብላቸውም ሳይገኙ መቅረታቸው ሲዘገብ ቆይቷል። በፍርድ ቤቶች አሰራር በቀጠሮው ችሎት ያልተገኘ ተከሳሽ በሀገር ቤት ከሆነ በፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ ከሀገር ውጭ ከሆነ ደግሞ በጋዜጣ እንዲጠራ የሚደረግ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ይህንን አሰራር በማለፍ ፋይሉን የዘጋበት ምክንያት አልታወቀም ። አቶ አብርሃ ደስታም የፍርድ ቤቱን የትዛዝ ጥሪ ያልተቀበሉበትና የገፉበት ምክንያትም ግልጽ አልሆነም። ፍርድ ቤቱ ፋይሉን የዘጋው ከ8ኛ ጥሪ በሗላ መሆኑም ተመልክቷል። ሆኖም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ድምጻቸው የጎላ የህወሃት ደጋፊዎች ኮለኔል ደመቀ ዘውዴ ከጎንደር አዲስ አበባ ተወስደው ካልታሰሩ፣አቶ አብርሃ ደስታም ወደ አዲስ አበባ መሔድ የለባቸውም ሲሉ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። አቶ አብርሃ ደስታ በአሁኑ ወቅት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸው ይታወቃል። አረና ፓርቲ የመድረክ አባል የሆነ ታቃዋሚ ድርጅት ነው። በችሎት ቀርቦ የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል የነበረው አቶ አቶ ዳንኤል ሺበሺም በነጻ መሰናበቱ ታውቋል።


No comments:

Post a Comment