(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 18/2009) በእነ መልካሙ ክንፉ የክስ መዝገብ ከወንድሙ ቦንሳ በየነ ጋር ከኦነግ ጋር ተባብራችኋል በሚል ክስ የቀረበበት አየለ በየነ ለዘጠኝ ወራት በማእከላዊ እስር ቤት መቆየቱን ጓደኞቹ ሐምሌ 18/2009 በዋለው ችሎት ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። የጸር ሽብር ህጉ ከሚፈቅደው ግዜ በላይ ተጨማሪ 5 ወራት በአጠቃላይ ዘጠኝ ወራት በማእከላዊ ምርመራ በእስርና በምርመራ ላይ መቆየታቸውን የገለጹት የወጣት አየለ በየነ አባሪዎቹ ህክምና ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ምግብ መመገብ ካቆመ ከ10 ቀናት በኋላ ተዳክሞ ወደ ህክምና ቢወሰድም ህይወቱን ማትረፍ አለመቻሉን ገልጸዋል። ትላንት ሰኞ ሐምሌ 17/2009 ሕይወቱ ያለፈው ወጣት አየለ ሆን ተብሎ ህይወቱ እንዲያልፍ መደረጉን ለችሎቱ የገለጹት አባሪዎቹ ለራሳቸውም ደህንነት እንደሚሰጉ ተናግረዋል። አውቀው ነው የገደሉት እኛንም ይገድሉናል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። አንደኛው ተከሳሽ መልካሙ ክንፉ እኛም ብንሆን ዋስትና የለንም ሲል ስጋቱን ገልጿል። ይህንን የሚያደረገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀን እንሙት ሲል 4ኛው ተከሳሽ ይማም መሀመድ መጠየቁንም ከኢሳት ምንጮች መረጃ መረዳት ተችሏል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የ29 አመቱ አየለ በየነ ሕይወቱ ማለፉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ወህኒ ቤቱ እንዲያቀርብ ለሐምሌ 26/2009 ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል። ታላቅ ወንድሙን በወህኒ ያጣው 3ኛው ተከሳሽ ቦንሳ በየነ አሁንም በወህኒ ሆኖ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ መሆኑም ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment