ሰኔ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብርና በሌሎችም ወንጀሎች ተከሰው በእስር ቤት እያሉ እንደገና ቂሊንጦን አቃጥለዋል በሚል ክስ ከቀረበባቸው ወጣቶች መካከል፣ የተወሰኑት ዝዋይ እስር ቤት ተወስደው ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል። እስረኞች ፍርድ ቤት ላይ ተቃውሞ በማሰማት፣ እንዲሁም የእስር ቤቱን አስተዳደር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ይታወቁ ነበር። በተለይ አዲስ ክስ በሀሰት ከተመሰረተባቸው በኋላና ክሱን ለመመስረትም ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በኋላ በድፍረት ፍርድ ቤት ላይ አቤቱታቸውን በማቅረብ፣ የእስር ቤቱን አስተዳደር ሲጋፈጡ ቆይተዋል። በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ የሽብር ክስ ከተመሰረተባቸው 38ቱ እስረኞች በተጨማሪ በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱት 121 ተከሳሾች ፍርድ ቤት አንቀርብም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አልቀበል በማለቱ፣ ዳኞችን የሕወሓት ኢህአዴግ ወኪሎች በማለት በግልጽ የተቹ ሲሆን፣ የ121 ሰዎች መዝገብ ተቀይሮ በ20 ሰዎች እንዲከፋፈል ከተደረገ በሁዋላ ደግሞ እስረኞቹ ፍርድ ቤት አንሄድም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል። ወጣቶቹን ለመወንጀል ሰበብ ሲፈልግ የነበረው ቂሊንጦ እስር ቤት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት እስረኞቹ እርስበርስ ተጣልተዋል በሚል የተወሰኑትን ወደ ዝዋይ ወስዷል፡፡ እስረኞች ለሁለት ቀናት ያክል ቀንና ሌሊት እጃቸው የፊጥኝ ታስረው በደል ተፈጽሞባቸዋል። ደቡብ ክልል እየተባለ በሚጠራው የዝዋይ እስር ቤት ክፍል ውስጥ ፣ በሮቹ የማይከፈቱ ሲሆን እስረኞች ሌት ተቀን ይደበደባሉ፣ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ስፖርት እንዲሰሩ እየተደረጉም ይቀጣሉ። ከቤተሰብ ጋር መገናኘትም አይችሉም፡፡ እነዚሁ እስረኞች በዚህ ክፍል ውስጥ ታስረው በተመሳሳይ ሁኔታ ቅጣት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ የእስር ቤቱ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ስቃይ የሚፈጸምባቸው እስረኞች ማንነት ተለይቶ እንዳይታወቅ ለማድረግ በቂሊንጦ ዞን 5 የሚገኙ እስረኞች በቤተሰብ እንዳይጠየቁ ተከልክለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከአማራ ክልል የተያዙ በርካታ ዜጎች ክስ እየተመሰረተባቸው ነው። በክልሉ የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ፣ የተያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሰሞኑን የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ120 በላይ ከአማራ ክልል የተያዙ ሰዎች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹ ክሳቸው ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር የተያያዘ ነው።
No comments:
Post a Comment