ሰኔ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህገወጥ መንገድ ወደ ታንዛኒያ የገቡ 45 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በበቆሎ ማሳ ውስጥ ተደብቀው መያዛቸውን የታንዛኒያ ባለስልጣናት አስታወቁ። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ካለምንም ሕጋዊ ሰነድ ወደ ታንዛኒያ ሲገቡ መያዛቸውን የታንጋ ክፍለሃገር የስደተኞች ጉዳይ ዋና ሃላፊ የሆኑት ክሪስፒን ኒጎያኒ ገልጸዋል። ባለስልጣኑኑ እንዳሉት ስደተኞቹ በሰሜናዊ ምስራቅ ታንዛኒያ በሚኪንጋ አውራጃ በኬኒያ እና ታንዛኒያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሆሮሆሮ ላይ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። አክለውም ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በእርሻ ማሳ ውስጥ ተደብቀው ከታንዛኒያ ወደ ማላዊ ድንበር የሚያሸጋግራቸውን ሰው በመጠበቅ ላይ እያሉ መያዛቸውን እና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊገቡ እንደነበርም አስታውቀዋል። ሕገወጥ ስደተኞችን በማዘዋወር ተግባር ላይ የተሰማሩ ታንዛኒያዊያን መኖራቸውንም ባልስልጣኑ አውስተው ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞችን በበቆሎ ማሳ ውስጥ ሲያዙ በርሃብ ደክመው መዛላቸውንም ባልስልጣኑ አክለው ገልጸዋል። በሕገወጥ መንገድ ወደ ታንዛኒያ በመግባታቸው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ እና ታንዛኒያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ሕገወጥ ስደተኞች መተላለፊያ አገር እየሆነች መምጣትዋን ዥንዋ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment