ሰኔ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እዳ አለባቸው የሚባሉ ነጋዴዎች በባንክ ያስመቀጡትን ገንዘባቸውን እንዳያወጡ እገዳ እየተጣለባቸው መሆኑን ነጋዴዎች ገልጸዋል። ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ገዢው ፓርቲ፣ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ጋር ያልተመጣጣነ ግብር እንዲከፍሉ በማድረጉ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ነጋዴዎች ምሬታቸውን እየገለጹ ነው። “ የሌለንን ገቢ እንዳለን አድርጎ የሚጣለው ግብር” በኑሮአችን ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው የሚሉት ነጋዴዎች፣ ብዙዎች የንግድ ፈቀዳቸውን ለመመለስ እየተገደድን ነው ይላሉ። በአዲስ አበባ ነጋዴዎች አቤቱታቸውን የሚሰማላቸው በመጣታቸው እየተቸገሩ ነው። የኢህአዴግ ካድሬዎች በበኩላቸው ነጋዴዎች ግብራቸውን ከከፈሉ በሁዋላ መከራከር እንደሚችሉ ለማሰማመን እየሞከሩ ነው። ይሁን እንጅ ነጋዴዎች፣ አጠቃላይ የግብር አጣጣል ዘዴው ካልተቀየረ በስተቀር በአቤቱታ ብቻ አይፈታም ይላሉ። በደቡብ ክልል በከምባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ ላይ ብዙ ነጋዴዎች በተጠላባቸው የተጋነነ ግብር ቁጣቸውን መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ነጋዴዎቹ ባልሰራነው ስራና ባላገኘነው ገቢ እንዴት ከፍተኛ ግብር ይጣልብናል በማለት አቤቱታ ቢያቀርቡም ፣ ተገቢውን መልስ የሚመልስላቸው አካል አላገኙም። አንዳንድ ነጋዴዎች ግብር አልከፈላችሁም በሚል በባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ መታገዳቸውንም ተናግረዋል። የግብር እዳ ያለባቸው ነጋዴዎች የባንክ ገንዘባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እግዱን የጣለው ክፍል ማን እንደሆነ በግልጽ ባልተገለጸበት ሁኔታ ባንኮች ገንዘብ ማገዳቸው ህገወጥ መሆኑንም ነጋዴዎች ተናግረዋል። በአማራ ክልልም እንዲሁ ነጋዴዎች ተመሳሳይ ቅሬታ እያቀረቡ ነው።
No comments:
Post a Comment