(ኢሳት ዜና — ሐምሌ 10/2009) በደብረታቦር በሕዋሃት/ኢህአዲግ አገዛዝ የታሰሩት ባህታዊ አባ ብርሃኑ ካልተፈቱ ሕዝባዊ ተቃውሞአቸውን ለመቀጠል የከተማዋ ነዋሪዎች ተስማሙ። የከተማዋ ከንቲባ የሕዝቡን ቁጣ በመፍራት ባህታዊው አባ ብርሃኑ ሐምሌ 12/2009 ባላቸው ቀጠሮ መሰረት ከእስር እንደሚፈቱ ማረጋግጫ ቢሰጡም የአካባቢው ነዋሪዎች የጀመሩትን ተቃውሞ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በደብረታቦር በኢየሱስ ደብር ቅጥር ግቢ ተራራማ ቦታ ላይ የቴሌቪዥን ታወር ነው በሚል ሲካሄድ የነበረው ግንባታም በሕዝብ ተቃውሞ እንዲቆም ተደርጓል። በታላቁ ደብር ኢየሱስ ቅጥር ግቢ በታቦተ ህጉ መውጫ ላይ ያለምእመናኑ ፈቃድ እየተገነባ ያለው ታወር የቴሌቪዥን ማሰራጫ ነው ቢባልም ላሊበላ አካባቢ ለተተከለው የራዳር የመረጃ ቋት ተጨማሪ ማስተላለፊያ መሆኑ ይነገራል። እናም ይህ ታወር ያለህዝቡና ሕዝበ ክርስቲያኑ ፈቃድ በደብሩ ውስጥ የተሰራ ስለሆነ ባህታዊው ካልተፈቱ እናፈርሰዋለን ሲሉ የአካባቢው ሰዎች ማዛታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ባህታዊ ብርሀኑ በአገዛዙ ከታፈኑበት ጊዜ ጀምሮ ምግብ አልበላም ብለው በጾምና በጸሎት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ባህታዊው የታሰሩት በሕዋሃት/ኢህአዲግ የሚመራው አገዛዝ አባ ሃይለማርያም የተባሉ የስርአቱ ደጋፊ የዞኑ ሀገረ ስብከት ተደርገው መመደባቸውን ሕዝቡ ከተቃወመ በሗላ ነው። ይህንኑ ተከትሎም በቤተክርስትያኑ አጥር ግቢ እየተገነባ ያለውን ታወር ሕዝቡ ለማፍረስ በመንቀሳቀሱ የአጋዚ ወታደሮችና የመንግስት ታጣቂዎች አካባቢውን መክበባቸው ተንግሯል። በደብረታቦር ከፍተኛ ውጥረት በመኖሩ አካባቢው በታጠቁ ፌደራሎች እየተጠበቀ ቢሆንም የሕዝቡ ተቃውሞ እያየለ በመምጣቱ የከተማው ከንቲባ ድርድርን እንደመረጡ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል። የደብረታቦር ህዝብ ባህታዊው በፍርድ ቤቱ ቀጠሮ መሰረት ሐምሌ 12/2009 ካልተፈቱ ወደ ከፍተኛ አመጽ እንደሚያመራ እየተጠበቀ ይገኛል።
No comments:
Post a Comment