Tuesday, September 13, 2016

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያላት አቅም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነገረ

ኢሳት (መስከረም 3 ፥ 2009)
የአለም ባንክ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያላት አቅም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንና ሃገሪቱ ከ189 የአለማችን ሃገራትይ መካከል በ148ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን ይፋ አደረገ። 
በአለም የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ዙሪያ ሪፖርቱን ያወጣው የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርገው የሚገኙ የውጭ ኢንቨስትመንት ደንቦችና ጥበቃዎች ከሌሎች ሃገራት ሲነጻጸሩ ደካማ ሆነው መገኘታቸውን ገልጿል። 
የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ህጎቻቸው ላይ የማሻሻያ እርምጃ ሲወስዱ ቢቆይም የኢትዮጵያ መንግስት በቂ እርምጃ ሳይወስድ መቅረቱ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረጉን የሃገሪቱ የልማት አጋር የሆነው ባንኩ በሪፖርቱ አመልክቷል።
ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሴኔጋል፣ ቤኒንና፣ ቆፕሮስ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የህግ ማሻሻያን አድርገው የተሻለ ውጤት ማስመዘባቸውን የአለም ባንክ በአመታዊ ሪፖርት አስፍሯል። 


የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአለም ባንክ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ንግድ ገቢን ለማሻሻል የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንድትወስድ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል።
ሃገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያላትን አቅም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ከተካሄደባቸው 189 አገራት መካከል ኢትዮጵያ ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየት በ148ኛ ደረጃ ላይ ልትፈረጅ መቻሏን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ሲንጋፖር፣ ኒው ዚላንድ፣ ዴንማርክ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ከአለማችን የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ለመያዝ የበቁ ሲሆን፣ ኤርትራ፣ ሊቢያና ደቡብ ሱዳን ከ189ኛ እስከ 187ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የአለም ባንክ የተለያዩ ወቅታዊ መረጃዎችን በግብዓትነት ተጠቅሞ ይፋ ያደረገው ይኸው ሪፖርት ለአለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አካላት ለመረጃነት እንደሚውልና የተቀመጠው ደረጃም ጠቃሚ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ለወራት ያህል በኦሮሚያ ክልል የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።
በቅርቡ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ጥቃት ደርስቦት የነበረ አንድ የኔዘርላንድ የአበባ አምራች ኩባንያ ከሃገሪቱ ለቆ መውጣቱን ይፋ እንዳደረገ መዘገባችን ይታወሳል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ተግባራዊ አድርጎታል ያሉት የመሬት ቅርምት በአርሶ አደሮች መካከል ተቃውሞ ማስከተሉንና፣ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ሰልፈኞች ድርጊት መነሳቱን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በኢንቨስትመንትና በቱሪስት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment