መስከረም ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
በአማራ ክልል ለተነሳው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መነሻ የሆኑት የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ በዛሬው እለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በአካል ሳይቀርቡ ለአምስተኛ ጊዜ ለመስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪ የነበሩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ አግባብ ውጪ ከቤታቸው አፍነው ሊወስዷቸው ሲሞክሩ እራሳቸውን ለመከላከል የአልሞትባይ ተጋዳይ ሆነው በሕዝቡ ትብብር ከሞት መትረፋቸው ይታወሳል። በወቅቱ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አባላት ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ኮሎኔል ደመቀ በጎንደር ከተማ ሕዝብ እና በከተማዋ ከንቲባ አማካኝነት በአደራ ተሰጥተው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ውሳኔ ሳይሰጣቸው በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ እየተመላለሱ ነው። የኮሎኔል ደመቀን የፍርድ ሂደት ለመከታተል ብዛት ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛው ፍርድ ቤት አካባቢ አስቀድመው ተገኝተዋል። ከሕዝቡ ቁጥር ባልተናነሰ የታጠቁ የአጋዚ ወታደሮች ከተማዋን ቢወሯትም በተለይ የከተማው ወጣቶች ካለምንም ፍርሃት በብዛት መገኘታቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
No comments:
Post a Comment