Thursday, September 15, 2016

በቂሊንጦ እስር ቤት በእሳትና በጥይት የተገደሉ ዜጎች ያለማስረጃ ለቤተሰብ እየተሰጡ ነው

ኢሳት (መስከረም 5 ፥ 2009)
በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት ደርስ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተገናኘ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ እስረኞች ያለምንም ማስረጃ ለቤተሰብ እንዲሰጥ በመደረግ ላይ መሆኑ ታወቀ። 
የማንነት ጥያቄን አስነስታችኋል ተብለው ባለፈው አመት ለእስር ተዳርገው ከነበሩት የሰሚን ጎንደር ዞን ትክል ድንጋይ ከተማ ነዋሪዎች መካከል በቂሊንጦ እስር ቤት ህይወታቸው ያለፈው አቶ ይላቅ አቸነፍ አስከሬን ለቤተሰብ ተሰጥቶ የቀብር ስነስርዓት መፈጸሙን ለኢሳት የደረሰ መረጃ አመልክቷል። 

የመንግስት ባለስልጣናት እስረኞቹ በእሳት ቃጠሎ እንደሞቱ ቢገለፅም፣ አስከሬን በጥይት የተመታ እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ለኢሳት ሲገልፁ ቆይተዋል። 
በቂሊንጦ እስር ቤት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ከ20 የሚበልጡ እስረኞች መሞታቸውን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ የእስር ቤቱ አስተዳደር ሁሉም አስከሬን ለቤተሰብ ይስጥ አይስጥ እስካሁን ድረስ የሰጠው መረጃ የለም።
የቤተሰብ አባሎቻቸውን አስከሬን በመቀበል ላይ ያሉ ሌሎች የቤተሰብ አባላት የተቀበሉት አስከሬን በጥይት ሰለመመታቱ ማረጋገጥ እንደቻሉ ለኢሳትና ለሌሎች መገኛኛ ብዙሃን ሲገልጹ መሰንበታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት የልጃቸውን አስከሬን የተረከቡ ሌላ አባት የተረከቡት አስከሬን እንዳይታይ ተደርጎ መቅበራቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል። በእስር ቤቱ የእሳት ቃጠሎ በደረሰ ጊዜ ያለትጥቅ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ የጸጥታ አባል እስረኞችን ያነጣጠረ የተኩስ ድርጊት ሲፈጸም መቆየቱን ይፋ ማድረጉም ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment