በባዕዳን በቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ ሀገሮች ሁለት ዋና ዋና ሀብታቸውን አጥተዋል።( በነገራችን ላይ በባዕዳን ቅኝ ግዛት የተያዙቱኑ ነው ያልኩት እንጂ ፕሬዝዳንት መሆን ያማረው ሁሉ ቅኝ ግዛት ነበርኩ እያለ የእራሱን እና የህዝቡን ክብር ገደል የሚጨምረውን አይመለከትም።)ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ካልተገዙ ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች።ኢትዮጵያውያንን ቡና አትጠጡ ቢራ ብቻ ጠጡ ብሎ ያስገደዳቸው ቅኝ ገዢ አልነበረባቸውም።እድሜ በደማቸው ሀገራቸውን አስከብረው ለኖሩት አባቶቻችን እና እናቶቻችን።እኛ እንደ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ዋና ከተማችንን የቅኝ ገዢዎች አልመረጡልንም። አለመምረጥ ብቻ አይደለም የከተሞቻችን ህንፃዎች እና መንገዶች በአብዛኛው የተሰሩት በእራሳችን መሀንዲሶች ነው።የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃቤት ፕላን ሲቀርብ አንድ ፈረንሳዊ መሃንዲስ ባለ ብዙ ፎቅ እንዲሆን አድርጎ አቅርቦ ነበር።በኃላ ግን ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ (ስማቸውን አላስታውስም) ወደ ንጉሡ ቀርበው ”ይህንን ያህል ፎቅ ብዙ ሕዝብ በእየለቱ በሚወጣበት እና በሚገባበት ህንፃ ላይ አይሆንም።ይህ ማለት ከሀገሩ ሊፍት እንድናስገባ ሊያደርገን ነው።ከእዝያ ይልቅ ወደጎን ነው መለጠጥ ያለበት” ብለው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ማዘጋጃ ቤቱ ወደጎን እንዲሰፋ ተደረገ።በእዚህም ብዙ ሕዝብ ለጉዳዩ በቀላሉ ለመውጣት እና ለመግባት ቻለ።ቅኝ ገዢዎች መሰረተ ልማቱን እንዴት ለሀገራቸው ኢንዱስትሪዎች መጋቢ እንዲሆን አድርገው እንደሚቀርፁ የሚያመላክት አንዱ ማሳያ ነው የማዘጋጃ ቤቱ ህንፃ ጉዳይ።
ቅኝ ግዛት መዘዙ ብዙ ነው።ጉዳቱ የሚታወቀው ትውልድ በተቀያየረ ቁጥር ነው።
ዛሬ ግን ያልገባኝ ጉዳይ በኢትዮጵያ የቢራ ፋብሪካ እንደ አሸን መፍላት ነው።በምግብ እራሷን ያልቻለች ሃገር ለምንድነው የእህል ቀበኛ የቢራ ፋብሪካዎች እንዲበዙላት የተደረገው? ብዙ ተመጣጣኝ ምግብ ማቀናበርያ በምትፈልግ ሀገር ውስጥ ለምን ለቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ይደረጋል? በኑሮ ውድነት በሚንገላታ ሕዝብ መካከል አማላይ የሆኑ የቢራ ማስታወቅያዎች ምን ይሰሩለታል? ቢራ ከሀገር ይጥፋ አይባልም።ሰው እንደ ምርጫው እና ፍላጎቱ ሊጎነጭ ይችላል።ግን እንደ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት ሊደከምበት አይገባም።የኢህአዲግ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ የቢራ ምርት ላይ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰሩ ይታያል።የቢራ ፋብሪካ መመስረት ብቻ ሳይሆን የማስፋፋት ሥራ በጣም እየተሰራበት ነው።በቅርቡ ወደ ገበያ ሊመጣ ነው የተባለው የራያ ቢራን ጨምሮ 8 የቢራ ፋብሪካዎች አሉ።እነርሱም አዲስ ቢራ፣በደሌ ቢራ፣ሐረር ቢራ፣ዳሸን ቢራ፣ሜታ ቢራ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ባቲ ቢራ እና በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ራያ ቢራ ናቸው።
ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (መጋቢት 4/2006 ዓም ወጥቶ የነበረ)
No comments:
Post a Comment