Friday, November 21, 2014

ምርጫ 2007ን ለመዝረፍ በሕወሃት/ኢሕአዴግ በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች የተደረጉ ወንጀለኛ ዝግጅቶች – በፓርቲው ውስጣዊ መረጃ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ

– “በተለይም በአሁኑ ሰዓት ፈተና ላይ የጣለን የምርጫ ጉዳይ እንደምናሸነፍ ቃል የተያዘበት ቢሆንም [ቃለ ጉባዔ/የፓርቲው ሊቀመንበር መመሪያ?]፤ ፈተናዎች የሚፈጠሩት በሕዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግሥት ክንፍ አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በዚህም ቀድሞ መዘጋጀት ያለበት እና ለሁከት እና ለብጥብጥ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው የሕዝብ ክንፍ የተማረው ሃይል ሊሆን ስለሚችል ሊታሰብ ይገባል ብለዋል [የፓርቲው ሊቀመንበር?]፡፡”

ምንጭ፡ በትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ አስተባባሪነት የተዘጋጀው:

“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢሕአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሠራዊት ግንባታ አድረጃጀት ማንዋል – ለምርጫ 2007”

ማጠቃለያ

ራሱ ሕወሃት/ኢሕአዴግም እንዳመነው፡ በከፍተኛ ፍርሃት እየራደ ያለ ባለአራት-ግንባሮችና ሌሎች አናሳ ቡድኖች ስብስብ ዋናው ሥልጣን በሕወሃት እጅ ሆኖ በኃይልና በከፍተኛ ጭቆና ሃገራችንን የሚያስተዳድር የፖለቲካ ድርጅት ነው። ከባህሪው የድርጅቱ ትልቁ ችግርም፡ ሣር ቅጠሉ ሳይቀር፡ ከዛሬ ነገ ሥልጣን ያሳጡኛል ብሎ በሥጋት የሚኖር በመሆኑ፡ ሣሩ፡ ቅጠሉንና ጎመኑም ጠላቶቹ እየመሰሉት፡ በእስር ቤት የሚያጉራቸው ወገኖቻችንን ብዛት ቤቶቻቸው ይቁጠሯቸው ብሎ ማለፉ፡ በቆጠራ ብቻ ጊዜ ከማባከን ያድናል።



ከላይ የተቀመጡት የፖለቲካ ድርጅቱን አስተሳሰብና ማንነት የሚጠቁሙት ጥቅሶች እንደሚያመለክቱት፡ ሌላው ቀርቶ፡ መከላከያውና የስለላው ዘርፍ ሃገር በሚያስተዳድርበት ሁኔታ እንኳ፡ አገዛዙ “በሕዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግሥት ክንፍ አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም” በማለት ስለመጭው ምርጫ ያለውን ሥጋት ያረጋግጥልናል፡፡

በታሪክ እንደታየው፡ አንዳንድ መሪዎችና መንግሥታትም በውናቸውና በእንቅልፋቸው ጠላት ካልፈጠሩ ሥራቸውን መሥራት እንደሚያስቸግራቸው ሁሉ፡ ዛሬ ሕወሃት/ኢሕአዴግም ክፉኛ እየተረበሽ በመሆኑ፡ ኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ባሻገርም እስትንፋስ ያለው ነገር ሁሉ ‘እያሴረብኝ ነው፤ ጠላቴ ነው’ ብሎ የሚያምንበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይህ ‘መንግሥታዊ’ መሸበር ምን ያህል ሃገራችንንና ሕዝባችንን ይጎዳ ይሆን? ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ፡ ይህ ሁኔታው የሚያስከትለው የሉዓላዊነት ሽያጭና ምንዘራ ይኖር ይሆን? በምርጫ ታኮ፣ ለብዙዎች ሕይወትስ መቀጠፍ እንደገና ሁኔታውን ያመቻች ይሆን? ቀደም ብለው በፖለቲካ ድርጅቱ የተጀመሩት ዝግጅቶች ይህንኑ በገሃድ የሚያመላክቱ ስለሆኑ፡ ለጥያቄዎቹ የኔም መልሴ የእነዚህ ሁኔታዎች ተፈጻሚነት ዕድሎች ካለመሆን ይልቅ ወደ መሆን ያመዝናሉ የሚል ነው!

እነዚህም ድርጊቶቹ በሕግጋት ጥሰት የተሞሉ በመሆናቸው፡-

(ሀ) የምርጫውን ውጤት ከምርጫው በፊት በመተንበይና ውጤቱም በኃይል አጠቃቀም፡ ለሕወሃት/ኢሕአዴግ እንዲመቻች መደረጉን በመረጃነት በመያዝ፤

(ለ) የሀገሪቱን ዜጎች (ወጣቶች፡ ተማሪዎች፡ ምሁራን፡ አብዛኛውን ሕዝብና ቢሮክራሲውን ወዘተ) በመለየት ለጥቃት እያዘጋጀ ሕዝቡንም ወደ እርስ በእርስ ግጭት እየገፋፋ በመሆኑ፤

(ሐ) ከአመራር በማይጠበቅ የማጭበርበርና ሌሎችም ሕገወጥ ተግባሮች፡ ለምሳሌ የሕዝብን የግብር ክፍያለራሱ የፖለቲካ ጥቅም የማዋል ወንጀሎች መፈጸሙን በማስመልከት ዜጎች መረጃውን ለሕዝብ እንዲጋለጥ ማድረጋቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም ይህንን ሕገወጥ ድርጊት ሕጋዊ ነው በማለት ባለፈው ጥቅምት፡ ፓርላማ ውስጥ አቋማቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል!

(መ) ወጣት ተማሪዎቻችን በሥነ ሥርዓት ትምህርታቸውን በመከታተል ዕውቀት ቀስመው ሃገራቸውን ወደፊት ለማስገስገስ እንዳይችሉ፡ ትምህርት ቤቶችን ለስለላና ለርዕዮተ ዓለም ማስፋፊያ በመጠቀሙ፣ በቤተስብና በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የምሥራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት ስታዚ በተጠቀመበት አንድ ለአምስት የስለላ አሠራር ቤተስቦችንና ሠራተኞችን በየፊናቸው አቆላልፎ (“The Stasi Octopus”

የወቅቱ አሳሳቢ ሥዕል

ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በርከት ያሉ ጸረ-ወጣቶች፣ ጸረ-ተማሪዎችና ጸረ-ምሁራን፣ የትምህርት ጥራትን አዳፋኝ የሆኑ፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን ብቁ የሰው ኃይል እንዳታፈራ የዘለቄታ መንገዷን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችና በአመራር አካላት የተዘጋጁ ጽሁፎች – አንዳንዴም እንደ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ጥናቶች ሌላ ጊዜ ደግሞ መመሪያዎች እየተባሉ – ገዥው ፓርቲ በቀጥታና በሚስጢር ለአባሎቹ ሲያሠራጭ ከርሟል። ይዘቶቻቸውም ሆነ ተጽዕኖዋቸው (impact) ምን እንደሆነ ለመረዳት ኮሜት ላይ ሮኬት ለማሳረፍ የሚያስችል ዕውቀት አይጠይቅም።

በተጨማሪም አንዳንድ ምንጮች (የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃዎችን ጨምሮ)፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚካሄዷቸው ጥናቶችና በዚህ ረገድ የውጭ ኤምባሲዎች የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች በአንዳንድ አነስ ያሉ ትምህርት ነክ የሆኑ የፖሊሲ ስብሰባዎች አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ አልፎ አልፎ ቀርበው፡ ለግንዛቤዎች ሠፊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እንዲሁም በየወቅቱና በየደረጃው በመነሻነት ወቅታዊ መረጃዎችንና የአገዛዙን አስተሳሰብ ስለሚያመላክቱ አሠራሮችና እርምጃዎችና ብዙ ጉዳዮች በኢሳት አማካይነትም ተደምጠዋል።

አሁን በያዝነው ወር “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢሕአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሠራዊት ግንባታ አድረጃጀት ማንዋል – ለምርጫ 2007” የተሰኘ ጽሁፍ ቀርቧል – እነርሱ ማንዋል ይሉታል። ‘ማንዋሉ’ በተማሪዎች ሥልጠና ወቅት እንደተፈለገው አልደረሰም። በተደጋጋሚ ታሽቶና ተፈትጎ ቢቀርብም፡ አሁንም ይዘቱ በቀረበበት መልኩ ጥቅም ላይ ሊውል የማይችል በባዶ የካድሬ ቃላት ክምችት የተሞላ ስካር፡ ዓላማው ግን ምርጫውን እንዴት ሕወሃት/ኢሕአዴግ አሸናፊ እንዲሆን ማስቻል በመሆኑ፡ እንደገና እንዲፈተግና ካልጸዳ ሽንፍላነቱ እንዲላቀቅ በሌሎች እንዲሻሻል ተደርጎ እንደገና ጥቅምት 2007 ቢቀርብም፡ ለአባላት እንኳ እንዲበተን ፈቃድ ያገኘው ከብዙ ማመንታት በኋላ ኅዳር 2007 ነው።

A mother grieving the assassination of her son by TPLF Agazi during the rally protesting theft of electoral results by the regime in 2005, where 193 people were mowed down within a few hours in Addis Abeba streets (Credit: BBC)

ያንን የተዘጋጀውን ‘ማንዋል’ ለማንበብ ዕድል በማግኘቴ እንደ አንድ ምሁር፡ በግልጽነት ልለው የምችለውና ካሰመርኩባቸው ጉዳዮች ይዘቶቹ መካከል ለተማሪዎችና ምሁራን ያዘለው ሊገነፍል የደረሰ ጥላቻና ቂም በቀል ግንባር ቀደም ሆነው ታይተውኛል። ከሁሉም የከፋ – ከምርጫ ማጭበርበር ባሻገር – በምርጫው ሰሞን ስለሚሚቀጠቀጡት፡ በአፈሳ ስለሚታሠሩት ወይንም ሊገደሉ ስለሚችሉ ወጣቶች ሚኒስትሩና ግብረ አበሮቻቸው ከወዲሁ ተጠያቂ ሊደረጉበት የሚገባ፡ አፈናና ግድያ እንዲካሄድ መመሪያ የሚሠጥ ሠነድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ምንም እንኳ ሃገራችን በዘመነ ሕወሃት/ኢሕአዴግ 31 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲኖራት ቢደረግም፡ ብዛት የጥራት መለኪያ ሊሆን ስለማይችል፥ በ2014 እና በ2013 ጽሁፎቼ፡ እነዚህ የከፍተኛ ትምህርቶች ተቋሞች ከዕውቀት ምንጭነት ይልቅ፡ ለሕወሃት የፕሮፓጋንዳ ማጥመጃ መረቦች መሆናቸውን ከማውቀውና ከሥጋቴ በመነሳት ችግሩን አስመልከቶ ሃሣቤን ለማካፈል ሞክሬያለሁ (http://ethiopiaobservatory.com/2014/08/20/2014-performance-ranking-of-ethiopias-31-universities-an-old-nation-being-reduced-to-beginner/ እናhttp://ethiopiaobservatory.com/2014/01/11/2013-performance-ranking-of-ethiopian-universities-in-both-african-and-global-metrics/)። ከትምህርቴና ከተለያዩ የሥራ መስኮች ከተቀስሙ ልምዶችና ግንዛቤዎች በመነሳት፡ በእነዚህ ጽሁፎችና በተያያዙ በሌሎችም አማክይነት (ለምሳሌም ያህል፡ Improving Education Quality, Equity and Access in Ethiopia፤Education under persistent attack in EthiopiaWhat a time, when education is openly made instrument for rights violation with TPLF requiring ‘certificate’ of support for its policies for entry to college ወዘተ) ለማሰማት የሞከርኩት ነገር ቢኖር፡ የሃገራችን ዩኒቨርሲቲዎችና የተማረ የሰው ኃይል ምርቶቻቸው በአሁኑ አያያዛቸው፡ ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ይቅርና፤ ኋላቀር ነው በሚባለው ሠሃራዊው አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጅች ጋር እንኳ ሃገራችን ተወዳዳሪ መሆን እንደተሳናት ነው።

ሁኔታዎች እንደሚያመላክቱትም ከሆነ፡ ችግሩ ከፖለቲካዊና ከአመራር ድንቁርናና ድህነት የመነጨ በመሆኑ፡ ለወደፊት እየተባባስ እንደሚሄድ ነው የሚተነበየው። ስለሆነም ለተረከበው ሃላፊነቱ ተጠያቂ የሚሆን መንግሥት እስኪመጣ ድረስ፡ ችግሩ ‘በነፕሮፌሰሮች’ ኃይለማርያም ደሳለኝ፡ ሽፈራው ሽጉጤ፡ በረከት ስምኦን፡ አባይ ፀሐዬ፡ ቴድሮስ አድሃኖም ወዘተ፡ የግልና የቡድን ሥልጣን ጥማት በተሳከሩና በጥቅም አሠራር በተመሠረተ አካሄድና አያያዛቸው የሚቀረፍ አይደለም።

በተለይም፡ ዩኒቨርስቲን የሚያህል ነገር፡ ያውም የዩኒቨርሲቲዎቹ ሴኔቶች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም እርምጃ ሊወስዱ ሲገባ፡ (የሌላቸው ዩኒቨርሲቲዎቹም እንዲኖራችው በማድረግ) እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ባለ ኋላቀር መሥሪያ ቤት ሥር ለተራ ጉዳዮች እንኳ አራት ኪሎ ማንኳኳትና ደጅ ጥናት የሚያስፈልግበት አስገዳጅ ሁኔታ – ተደርጎ በማይታወቅ አሠራር – በተለይም ስለ አስተዳደሩ፣ ሥራ ካሌንደሩና ካሪኩለሙ ምንም ዐይነት ስሜት፣ ብቃትና ግንዛቤ በሌለው/በሌላቸው ግለሰቦች እንዲመራ መደረጉ አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው።፡

መለስ ብለን እንኳ ስንመለከት፡ የአማራ ብሄረስብን አባሎች ሃገራቸው ውስጥ በፈቀዱት አካባቢ የመኖር ሕጋዊ መብት የሌላቸው ዜጎች በማስመሰል በፊርማው ከጉራ ፈርዳ ባባረረ ግለስብ መዳፍ ሥር የሃገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ አተገባበርና አፈጻጸም ከመውደቁ በላይ ለዕውቀት ውርደትና ለሃገራችንም ዘለቄታ ከዚህ የከፋ ነገር የለም።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለማስታወስ ያህል፡ ባለፈው ነሐሴ እንደተነገረው፡ ዩኒቨርሲቲዎች ለፓርቲው ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ተገዥ ያልሆኑትን ተማሪዎች ተቀብለው አንዳያሰተምሩ መከልከሉ፡ ትምህርት ለመስጠትም በራቸውን የሚከፍቱበትን ቀን ሳይቀር ገዥው ፓርቲና ትምህርት ሚኒስቴር የሚወስኑበት ሁኔታ መፈጠሩ፡ የዩኒቨርስቲዎቻችን ራስ ገዝነት ደብዛ ማጥፋትና የሚስጡት ትምህርት መሪዎቹ ራሳቸው በቅጡ ባልሰነቁት ርዕዮተ ዓለም መጨመላለቁ፣ ምን ያህል የትምህርትን ምንነንት ያጎድፈና ዕውቀትን የሚጻረር ድርጊት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።

Education Minister Shiferaw Shigute (Credit: Addis Fortune)

በአጠቃላይ፡ በተለይም ከሐምሌ 2014 ጀምሮ በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ሲካሄድ የነበረው እጅግ ተቃውሞ የበዛበት፣ ሕዝብ የተፋውን የገዥውን ፓርቲ ፖለቲካና ርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከትና የታሪክ ጥገና በስነጋ ለመጋትናመድረኩም በአብዛኛው ጸረ-ኢትዮጵያ ታሪክና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት እንዲሆን በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥረቶችንቀለማቸውን ባልለወጡ የኢትዮጵያ ልጆች በሃገራችን ላይ ስለተቃጣው ደባ ምንነትና ጥልቀት ለወጣቶቻችንና ለኢትዮጵያ ሆኖ ጥሩ ግንዛቤ የሚፈጥር መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።
የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ፥ ምንነትና ለምን?

ለዚህ ጉዳይ አስፈላጊነት መንስዔ የሆነው፡ ባለፈው ሐምሌ ወር፡ ከዚያ በፊትም በተበታተነ መልኩ – ክምርጫው መቃረብና ሕወሃት/ኢሕአዴግም በሕዝቡ በአብዛኛው ከመተፋቱ አኳያ – የመለስ ዜናዊ ተክል የሆኑት የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሠ፣ በፓርቲው የሥልጠና ኃላፊነታቸው – “የልማት ሠራዊትን” አቋቁሞ የፓርቲውን የበላይነት በቀበሌ፡ በገበሬ ማኅበር፡ በትምህርት ቤቶች፡ በዩኒቨርስቲዎች፡ በፋብሪካዎች ስለማፋፋም አስፈላጊነት “የኢሕአዴግን ተቃዋሚ ኃይላት ማንኮላሻ አቅም ግንባታ እና የአመራር ግንባታና የትራንስፎርሜሺን ጉዞ” በሚል ጽሁፍ አማካይነት አመራሩን ለማሳመን በመቻላቸው ነው።

የጥናቱ መግቢያ ላይ የመጀመሪያውን አንቀጽ ያነበበ ሰው ጭንቅላት ውስጥ መጀመሪያ የሚከሰተው፡ ሕወሃት እንደዛተው፡ ኢትዮጵያን ማፈራረስና መበታተን ሊችል ነውን የሚለውን ቁጭት የተመላውን ጥያቄ ነው። ይህም አንቀጽ እንዲህ ይላል፦

“አገራችንን በፈጣን ቀጣይነት ያለውና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት የዕዴገት ጉዞ ከዴህነት አላቆ በተራዘመ ሂደት ከበለጸጉት ሃገሮች ጎራ ለማሰለፍ፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ዓላማ፣ ስትራተጂ ስሌቶችና ፖሊሲዎችን መቀየስ ይጠይቃል፡፡ በሌላ አነጋገር አቅጣጫውን በትክክል የሚያመለክት መስመር መቀየስ የትራንስፎርሜሺን ስኬት የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ መስመሩን ለመቀየስ ይህንኑ ማድረግ የሚችል ብቃት ያለው አመራር ይጠይቃል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ፈተና ውስጥ ነው፡፡ ለአብነትም እነ አቶ መላኩ ፈንታን ማንሳት ይበቃል፡፡ ይህን ተከትሎል በአገሪቱ ያሉ አመራሮች ለመቀበል አለመቻላቸው እና የኡመድ ኡቦንግ ሃገር መክዳት፤ በጋምቤላ ክልል አመራር ያለው ታማኝነት አስተማማኝ አለመሆኑ፤ የአማራ ክልል አመራሮች ከግንቦት ሰባት ጋር የተያያዘ አመራር መገኝት ፤ የኦህዴድ አመራር ከኦነግ ጋር ማበር እና በአማራ ላይ የደረሰውን በደል በቸልታ መመልከት፤ በአሁኑ ስዓት በትግራይ፤ በቢንሻንጉል ጉምዝ (የአመራሩ ቸልተኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ)፤ በአፋር፤ በሶማሌ እና በሐረሬ ምርጫውን ማሸነፍ የሚችል አመራር ዴምፅ የማግኝት ዕዴል አለው፡፡ መስመሩ ከተቀየሰ በኋላ የትራንስፎርሜሺን ትግል በውል ይመራል እንጂ አይጠናቀቅም ቢባልም፣ በስጋት በተቀመጡ ክልሎች አሁንም አፋጣኝ ሥራ ካልተሠራ ኪሳራ ሉያመጡ ይችላል፡፡ ዓላማውን ለማሳካት የስትራተጂውን ኃይሎች ለማብቃትና በአግባቡ ለማሰለፍ የሚችል ብቃትና ቀጣይነት ያለው አመራር ይጠይቃል፡፡”

ይህ ጥናትም በኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላለው አስፈሪ ሁኔታ እንደመውጫ ቀዳዳ በመታየቱ፡ እያንዳንዱ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣንና የሕዝብ መገናኛ፡ የአቶ አዲሱ ጥናትን ባለፈው ነሐሴና መስከረም ውስጥ ሕዝቡ ቋቅ እስኪለው ድረስ ሁሉም አንድ ዐይነት ነገር ደግመው ደጋግመው በመጥቀስ፡ እንደ ጀማሪ ቫዮሊኒስቶች ኮንሠርት ወይንም የቁራዎች ጩኸት ለፖለቲከኞች ፍሬ ከርስኪ ማደናቆራቸው፡ የሥልጠናዎቹ ታዳሚዎች፡ በተለይም ተማሪዎች፡ ከመሰላቸትና ትዕግስታቸው በመሟጠጡ፡ የድፍረት ቃላት ልውውጦች በየሥልጠናው ስለመካሄዳቸው – ብዙዎችም በሰበብ አስባቡ ስለመታሠራቸው – ኢሳት በንቃት በመከታተል ‘ሙድና’ ሙቀቱን ሲያስጨበጠን እንደከረመ ይታወሳል።

ከላይ የተጠቀሰውን የአቶ አዲሱን ጥናት አስተከትሎ፡ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ለመላው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ተቋሞች፡ ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችለው ዝግጅትና ስትራቴጂ ቀይሰው ዝግጅታቸውን እንዲያቀርቡ፣ ሥልጠና እንዲያካሄዱ እንዲሁም የተቻላቸውን ያህል በመደራጀትና የአባላት ምልመላ ላይ ርብርብ እንዲጀምሩ ጥብቅ መመሪያ በማዕከላዊ ደረጃ ተላለፈ።

በዚህም መሠረት፡ የሴክተር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶችም በየዘርፋቸው የፓርቲ አባሎቻቸውን አስተባብረው በሚያዝያ 2007 ምርጫ፡ ብሎም ለዘለቄታው ድል – መለስ ዜናዊ እንዳለመው – ሕወሃት/ኢሕአዴግን በትንሹ ለ50 ዓመታ አገዛዝ ለማብቃት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ በዜና ማሠራጫዎች ጭምር ሲናፈስ ከርሟል።

ይህንን የሥራ ድርሻ በሚኒስትር ሽፈራው አማካይነት ትምህርት ሚኒስቴር እንዲያከናውን ከበላይ አካል ለአፍታ ሊዘነጋ የማይችል መመሪያ ደርሶታል። ሚኒስትሩም ብዙ የደክሙበትንና እየታሸ ሲመለስላችው ክርሞ አልጸዳ ያለውን የጥረታቸውን ውጤት – “የትምህርት ሠራዊት” – ሲያቀብጣቸው ሽፋኑና አርዕስቱ ላይ ‘ማንዋል’ብለውት ብዙ እንዲጠብቅበት አድርገው፡ ዓላማውን በሚገባ ቢገልጹም፤ የሚፈለገውን ማበርከት ሳይችኩ ቀርተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ አባባል ከሆነ፡ አቶ ሽፈራውና የሚመሩት ኮሚቴ ከፓርቲው አመራር አካል፡ ማለትም ከፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ስለምርጫ ድል አንድ መተማመኛ ተሰጥቷቸዋል። በአቶ ሽፈራው አገላለጽ፡ ምንም እንኳ በተለይም በአሁኑ ሰዓት የምርጫ ጉዳይ “ፈተና ላይ የጣለን ቢሆንም…እንደምናሸነፍ ቃል የተያዘበት” በመሆኑ፤ ዝግጅት ማድረግ ያለብን “ለሁከት እና ለብጥብጥ መሣሪያ ሊሆን የሚችለው የሕዝብ ክንፍ የተማረው ኃይል ሊሆን ስለሚችል” በጥብቅ ሊታሰብበት እንደሚገባ መመሪያ እንደተሰጣቸው ነው፡፡

በካቢኔ አባልነታቸው እንዲህ ማድረግ፡ ዛሬም ባይሆን ነገ በሕግ ያሰጠይቃል ለማለት ስብዕናውም ሆነ ድፍረቱ ወይንም ዕውቀቱ ስለሌላቸው፡ ሚኒስትሩ ያተኮሩት ገና ምርጫው ሳይደርስ ተማሪዎችን ቀድም አድርጎ መምታት ላይ ነው። ለምን ሲባሉ፡ የራሳቸው የሆነ ስለተማሪዎች አንድ ምክንያታዊ አመለካከት አላቸው። የእርምጃቸውን ትክክለኛነት ለማስጨበጥም – የራሳቸውን ግብ ፊታቸው ደቅነው – ከወጣቱ፡ ከተማሪውና ምሁሩ ባህሪ ተነስተው የደመደሙ ይመስል፡ እንዲህ ይላሉ፦

“የዩኒቨርስቲው/የተቋሙ/ የመማር ማስተማር፤ ምርምር፤ የአገልግሎት አሰጣጥና የዱሞክራሲ ሥርዓት መጎልበትን የተማሪዎች ውጤትና የባህሪ መሻሻልን አጀንዳ አንግበው እንደ አንድ ሠራዊት ለስኬቱ የሚረባረብ የጋራ ተልዕኮና ዓላማ ያለው ኃይል በማፍራት አቅም መፌጠርን ይጠይቃል፡፡ [ነገር ግን ወጣቶቹ] በኢሕአዴግ ላይ ያላቸው አቋም የወረደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በማንኛውም ተቃውሞ ድምፅ ከተጠሩ፤ ሰልፍ የሚያደምቁ፤ ተቃውሞን ከግብ ለማድረስ ሁነኛ መሣሪያ ናቸው፡፡ ተማሪዎች በየትኛውም ሃገር እንደታየው አደባባይን የመያዝ ሕዝብን አሰተባብረው ለተቃውሞ የማሳደም ዕድላቸው የሠፋ በመሆኑ፡ ከዚህም ሲያልፍ፤ የኢሕአዴግ ምከታን በመቃወም ለጠላት ጎራ ተሰልፌው የመታጠቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው/በተቋሙ/ማኅበረሰብ የትምህርት ልማት ሠራዊቱ የሚፈጠርበትና ሚናውን በመጫወት የትምህርት ሴክተሩን የትራንስፍርሜሽን ዕቅድ ማሳካትና በፖለቲካ ስብዕናቸው የተገነቡ ኢሕአዴግን የሚቀበሉ አድርጎ ማውጣት የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታውን አስፈላጊነትና አማራጭ የሌለው ስልት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡”

ስለዚህ ሚኒስትሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ውስጥ ከስለላ ድርጅቱ ጋር በመተባበር የተደራጁትና የሚደራጁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት “የትምህርት ልማት ሠራዊት”(የመንግሥትና የሕዝብ ክንፎች)” የብጥብጥ እና የሁከት መንስኤ የሆነውን ተማሪ በኢሕአዴግ አመራር አባላት እየታገዙ…በምርጫው ሊፈጠር የሚችለውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከት እና ብጥብጥ ለማሰቆም” ያስችላል ይላሉ።

ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ እስከ ግንቦት 2015 መፈጸም የሚገባቸው ነገሮች፡ ከረዥም ጊዜ ግቦች ጋር ተቀላቅለው አንባብያንን ብቻ ሳይሆን፡ እራሳቸውንም ግራ እንዳጋቡ ማየት ይቻላል። ለምሳሌም ያህል ጥናቱ ከተሰጠው ስያሜ በመነሳት፡ ትኩረቱ ድርጅታዊ፡ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሆኖ ሳለ፡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስለትምህርት ጥራት አስፈላጊነት ለመፖትለክ ዳድቷቸው በዚህ ‘ማንዋል’ ውስጥ ብዙ ሲውተረተሩ ይታያሉ።

በዚህም ምክንያት፣ 23-ገጽ በሆነው ማኑዋላቸው ውስጥ የትምህርት ጥራት 17 ጊዜ ተጥቅሷል። ብዙ ለሕዝብ የሚቀርቡ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ሠነዶች ውስጥ፡ የዚህ ዐይነቱ አቀራረብ ዓላማ፡ ሥውር የሆኑ እነርሱ የሚያተኩሩባቸው ነገሮች በአንባብያን እንዳይታዩ የሚደረግ ጥረት ነው። ዓላማቸው ያ ካልሆነ፡ ለምንድነው በዚህ ማንዋል ውስጥ የትምህርት ጥራት ጉዳዮች የተካተቱት? ከብዙዎቹ ዕጦቶች መካከል – ለምሳሌ ያህል – መጻሕፍት፡ ብቁ አስተማሪዎች፡ ላቦራቶሪዎች፡ በነጻነት የመማርና ማሰብ ሁኔታዎች በሌሉባቸው ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ውስጥ፡ የልማት ሠራዊት ምንደነው የሚፈይደው? ለትምህርት ሚኒስትሩ ግን እነዚህ ቅንጦት መስለዋቸው እንደሆን አይታውቅም፡ ሰለ ትምህርት ልማት ሠራዊት እጅግ አስፈላጊነት እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ፦

በሃገራችንም የተለያዩ የለውጥ መሣሪያዎችን በመጠቀም የተገኙ ልምድችን በመቀመርና በማስፋፋት አበረታች ውጤቶች የተገኙ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የትምህርት ሽፋንን ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን እንደ አንድ አብይ ውጤት መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ይታመናል፡፡ ይህንን እውን ለማዴረግ መከናወን ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ በትምህርት ሴክተሩ መዋቅር ውስጥ የተሟሟቀና የተደራጀ የትምህርት ልማት ሠራዊት በማቀጣጠልና በማስቀጠል የሠራዊት ግንባታ ሂደቱን በአስተማማኝ መሠረት ላይ መጣል ቁልፍ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀስው ሃሣብ ብዙም በገጾች ሳንርቅ፡ በተመሳሳይ መንገድ፡ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሚመራው ኮሚቴ የትምህርት ጥራት እንዴት ከምርጫው ጋር እንደተያያዘ ሳይገለጽ፡ የሚከተለውን ለአንባቢ ካድሬዎቹ ለማስጨበጥ ይሞክራል፦

“በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደትን በሚመለከት የተሟላ ግልጽነትን በመፍጠር ወጥነት ያለው የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት የልማት ሠራዊት ግንባታን ወይም የፖለቲካ ሠራዊት ግንባታ በሁለም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ በማቀጣጠልና በማስቀጠል ተቋማዊ ለውጡን እውን በማዴረግ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን፤ ምርጫ 2007 ውጤታማ ለማድረግና የኢሕአዴግን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ነው፡፡”

የትምህርት ሚኒስትሩ ዋናው ችግራቸው፡ የሚያደራጁት የኢሕአዴግ የምርጫ የድል ልማት ሠራዊት ግልጽነት የጎደለው መሆኑን በግልጽ ተጣራሽነት ይናገራሉ። እንዲሁም፡ ተልዕኮውን ተግባራዊ ለማዴረግ የሚያስችለው የአመለካከትና የክህሎት ትጥቅ ያልያዘ ስለመሆኑ በገሃድ ማመናቸውም አንድ ቁም ነገር ነው፡፡ ሆኖም፡ የምርጫ ድል ሠራዊቱን “ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ” ለማምራት “የሚያስችለው ቁርጠኝነት” የለውም የሚል ምስክርነት እየሰጡ፡ ይህንን በእርሳቸው ኃላፊነት ሥር የሚደራጀውን ድል አስረካቢ እንዴት ከምርጫው በፊት በቀሩት ስባት ወራት ሊለውጡት እንደሚችሉ ግን የሚሰጡት ሃሣብ የለም፡፡

ስለሆነም፡ ይህ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ፡ እርሳቸውን ምርጫው ከባድ “ፈተና” ውስጥ እንደጣላቸው ቢናገሩና ቢማረሩ፡ እምብዛም አያስገርምም! በልባቸውም፡ አቶ አዲሱ ለገሠን መለስ ዜናዊ በሕይወት ሳለ በጡረታ ተገልለው፡ ሞቱን ተከትሎ ክተሰናበቱበት ሕይወት በባህር ዳሩ ዘጠነኛ ጉባዔ ወቅት ወደ ሥራ ዓለም፣ ኃላፊነትና ሙሉ ደሞዝና የፓርቲ/የመንግሥት የሥልጠና ባለሥልጣንነት የመጡበትን ቀን ሳይረግሙ አይቀሩም!
የቻይና ባህላዊ አብዮት ለሕውሃት/ኢሕአዴግ ከረመጥ መውጫ ሲሆን

አቶ አዲሱ ለገሠ በጥናታችው ወስጥ የቻይናን ባህላዊ አብዮት (Cultural Revolution) ታሪክ ሕውሃት/ኢሕአዴግን ላጋጠሙት ችግሮች እንደ መፍትሄ መጠቀማቸው የአደባባይ ሚሥጢር ነው – በአባባልም፡ በዓላማም፡፡ በዚያ ፈታኝ የኤኮኖሚና የሕልውና ችግሮች ውስጥ ማኦን ላጋጠሙት ክሥልጣን የመገፋት አደጋ የልማት ሠራዊት፡ የተለያሉ ብርጌዶች፡ የወጣት አብዮታውያን ማኅበራትና ሌሎችንም በማቋቋም ጠላቶቹን መምታት ግድ ሆኖአል- የኤኮኖሚ ችግሮቹን ለመፍታት ባይረዱም።

ዛሬ ሕወሃት ለደረሰበት መተፋትና ፈተና እንደ መፍትሄ እነዚህን ዘዴዎች መጠቀማቸው፡ እምብዛም አያስገርምም። ይህንን የምልበትም ምክንያት፡ የፓርቲው የሥልጠና ጉዳይ ኃላፊው – ከላይ ከተጠቀሰው ጥናታቸው ለመገንዘብ እንደሚቻለው – በይዘቱ ቻይና ውስጥ ከ1966-1976 ተካሂዶ በአሥር ዓመታት ውስጥ ለብዙ ምሁራን መታሠርና መደምሰስ፡ ለብዙ ሚሊዮኖች መሰደድ መንስዔ የሆነው “ባህላዊ አብዮት” በሃገራችን በአንድ መልክ ለመጀመር የታቀደ ይመስላል።

የሚያስገርመው ነገር፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ይህ ነውጥ ያስፈለገበት ምክንያት ከ48 ዓመታት በፊት ቻይና ውስጥ የማኦ ዜቱንግ ሥልጣን የሃገሪቱ የኤኮኖሚ ድቀት፡ በተለይም ፖሊሲው ከተመሠረተበት The Great Leap Forward አለመሳካትና ውድቀት ጋር የተያያዘና በዚያ ትልቅ ሃገር ውስጥ ድህነት፡ ርሃብና እርዛት ተስፋፍቶ ቻይኖች ምንም ዐይነት ነገር የማይጸየፏና እንደ ምግብ እንዲመለከቱ አስገድዷል!

ከዚህም በላይ፡ ኅብረተስቡ ውስጥ ምሬትና ቁጣ ተበራክቶ፡ አንዳንድ የኮሚኒስት ፓርቲውና የወታደሩ ክንፍ ማኦ ላይ ዘመቻ መጀመራቸው ስለተደረስበት፡ ማኦ የነበረው ምርጫ ሳይቀደም መቅደም በመሆኑ፡ ባህላዊ አብዮት ጠላቶቹን ለመምታት የተጠቀመበት መሣሪያ ነበር።

አቶ አዲሱ ከዚህ – ቋንቋው እንኳ ሳይቀር (“ማፋፋም”፡ “ማቀጣጠል” “ፖለቲካዊ ትግል”፡ “ባህላዊ ለውጥ”፡ “መላውን ሕዝብ ከዳር ዳር ማነቃነቅ” ወዘተ) ከቻይና የባህል አብዮት የተዋሱት ሃሣብ፣ ዋና ዓላማው ሕወሃት የተነሳበትን ሕዝብና የሚወጉትን ኃይሎች ከበር ለመመለስ ያላቸው ምርጫ ሆኖ በመታየቱ ይመስላል።

መደምደሚያ

የወደፊቱን አስተካክሎ ማየት ለብዙ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባልሥልጣኖች ከባድ ቢሆንም፡ እንደ “እንደብድብ”፡ “እንሠር”፡ “እንምታ”፡ እንደ “እንግደል” ግን የሚቀላቸው ነገር ያለ አይመስልም።

የትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣኖችም፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለመጠበቅና ምርጫውን በአሸናፊነት ለመወጣት ሕጋዊ የሃሳብ፣ የዓላማና ድርጅታዊ ፉክክር አልከሰትላቸው ብሎ፡ ከሚኒስትር ሽፈራው ሽጉጤ ጥናት እንደተመለከትነው፡ አስፈላጊው ቀዳሚ ዒላማቸው፣ ወጣቱንና ምሁሩን የመምታትና የመደምሰስ ስምምነት ያደረጉ ይመስላል።

በመሆኑም፡ አቶ ሽፈራው ከዚህም ሆነ ከሌሎች ንግግሮቻቸው ለመረዳት እንደተቻለው፡ ወቅቱን የሚያቆይላቸው (safeguarding the status quo) ማናቸውም እርምጃ ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ። የ2007 ምርጫን አስመልክቶም፡ ግቡም ተጨባጭና በእጅ ሊያዝ የቀረበ አድርገው ይመለከቱታል።

በሌላ በኩል ደግሞ፡ አቶ አዲሱ ጥናታችው ውስጥ አንድ ቁም ነገር ይመሰክራሉ። ይኸውም፡ ኢትዮጵያን ወደ በለጸገች ሃገር ለመለወጥ ብቃት ያለው አመራር ብቻ ሳይሆን፡ ቀጣይነትም ያስፈልገዋል ይላሉ። በሌላ አባባል፡ የገዥው ፓርቲ ችግር፡ አሁን ሁለቱም የሉትም ነው የሚሉት፡፡ ይህንን ሁኔታ ቆጠብ ብለው እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፦

“በከተማም ያለው አባላችን ከትምህርት ዝግጅቱ ወዘተ አኳያ ሲታይ ሙያተኛ አመራር የመሆን ዕዴሉ ከአርሶ አደሩ የሰፋ ሆኖም፣ ከጥቂቱ በስተቀር በየሥራ መስኩ የሚቀጥል እንጂ ሙያተኛ የፖለቲካ መሪ ሆኖ የመሰለፍ ዕድል የሌለው ነው፡፡”

ለምን ለሚለው ጥያቄ መልስ ባይሰጡም፡ ኅብረተስቡን በነፃነትና ያላንዳች ማስገደድ ምን እንደሚፈልግ ያለመጠየቁን ጉዳይ አያነሱትም። እስከምናውቀው ድረስ፡ ሕዝቡ የሚለው አትርገጡኝ፡ አትናቁኝ፡ ራሴ በምፈልገው መንገድ ልደራጅ፡ አጭበርባሪዎችና ዘራፊዎች አልወድም ነው። ይህ ደግሞ ለሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚያስኬድ መንገድ አልሆነም። በመሆኑም፡ ዛሬም እንደትላንቱ፡ ይህ ሁኔታ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንንና ሥልጣኑን በያዙት ሰዎች መካከል ትልቁ የልዩነት ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል – መጭውን ምርጫ በሚመለከት።

ሌላው ቀርቶ፡ የገዥው ፓርቲ ሰዎች (think tanks) የሚጽፏቸውን ጥናቶች ስመለከት፡ ግርም የሚለኝ፡ በዚህ ዕጦትና ጽልመት ውስጥ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ለልማት ሠራዊት አባላት አመራርና አደራጅነት ያሠለጠናቸውንም የፓርቲውን አባላትም አስመልክቶ – እንደ ትምህርት ሚኒስትሩ ሁሉ – አቶ አዲሱም ሠፋ ስላለውና ትልቁ “የልማት ሠራዊት” ግንባታ ያጋጠመውን ችግር በመገምገም፡ ተስፋቸው ዝቅተኛ መሆኑን ለመሸፋፈን ቢሞክሩም፡ ከሞላው የተረፈው አምልጧቸው፡ እርሳቸውም ግምታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጥናታቸው ውስጥ አሥፍረውታል።

ይህ የትናንቱና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አብዮት ሪአልቲ ነው! ለመሆኑ የት ይሆን አብዮት የምኞታቸውንና የታገሉለትን ያ ክቡር ዓላማ ፍሬ አፍርቶ ሰዎች በዕድሜያቸው ለማየት የበቁት? ፈረንሣይ? አሜሪካ? ሩስያ? ቻይና? ኩባ? አብዮታዊ ዴሞክራሲ? አልመስለኝም! ከሌሎቹ ለመማር ችሎታ የተነፈግን ይመስል፡ ታዲያ ለምን ይሆን ዛሬም የአብዮት አስፈላጊነት ለኢትዮጵያውያን የሚስበክልን?

ስለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሥራ ድርሻ ስናስብ ለቁጥር ድርሻ – ትምህርት – ትርጉሙ ሕንጻ ገንብቶ ሕጻናት ራስ በራስ ከማፈጋፈግ ውጭ – የዛሬይቱ ኢትዮጵያ “እነዚህ ልጆች ምን ተማሩ?”፥ “ካለፈው ዓመትስ ወዲህ ትምህርት ምን ያህል አሳደጋቸው?” ወዘተ ብላ ለመጠየቅ ጊዜው፣ ፍላጎቱም የሌላት “ዲሞክራሲያዊት ሃገር” መሆኗ፣ የሕፃናቱን የወደፊት ተስፋ ሥልጣን ሲገፋው፤ ከላይ ባነሳኋዋቸውና ተመሳሳይ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ድህነቶች ምክንያት፡ ሃገራችን ብትሮጥም ቆማ መቅረቷን ሳስብ ሁለንተናዪ በፍርሃት ይርዳል!።


No comments:

Post a Comment