Friday, November 21, 2014

የባዮሎጂ ምሩቁ ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም ለሕክምናው ሞያ ያለውን ባይተዋርነትና ንቀት በድጋሚ አረጋገጠ!

ዶ/ር ቴድሮስ ከአንድ አለማቀፍ የሚድያ ተቋም ጋር አደረገው በተባለው ቃለ መጠይቅ “ኢቦላ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ በቀላሉ ቁጥር ላይ እናውለዋለን፤ ምክንያቱም በደምብ የተደራጀ የጤና ልማት ሰራዊትና የኤክስቴንሽን ፓኬጅ አሰራር ስላለን” ማለቱን ተነግሯል፡፡
እግዚሀር ይይላችሁ፡፡ ዐለምን ሁሉ ያስጨነቀው ኢቦላ በጤና ኤክስተንሽን ሰራተኞች ሊቆጣጠር!

ዶ/ር ቴድሮስ የባዮሎጂና የፐብሊክ ሀልዝ ባለሙያ በመሆኑ ማስመሰልና ደፍረት እንጂ ይህ ነው የሚባል የሕክምና እውቀት ያለው ሰው ሆኖ አያውቅም፡፡ በሀገሪቱ ያለውን የሕክምና ትምህርት ጥራት እንዲሞት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረና በኢትዮጵያ ሐኪሞች ዘንድ እጅግ የሚወቀስ አስመሳይ ሰው ነው፡፡



ዶ/ር ቴድሮስ ፓርላማ ላይ ቀርቦ “የሕክምና ሙያን ለማስተንፈስ “flooding “ የሚባል ፕሪንሲፕል እንጠቀማለን፡፡ ይኸውም በመላው ሀገሪቱ ባሉ የኒቨርሲቲዎች እስከ 9000 የሕክምና ተማሪዎች እንዲቀበሉ በማስገደድ ትምህርት አገኙ አላገኙ ብቻ ዶክተር አድርገን እናስመርቃቸዋለን” ብሎ የሚናገር ሰው ነው፡፡ በውጤቱም ይኸው በነርሶች የሚማሩ ሐኪሞች እየተፈበረኩልን ነው፡፡ ለዚህ ዐይነተኛ አብነት ዐዲግራት ዩኒቨርሲቲ ላይ ሶስተኛ ዐመቱ የያዘ የሕክምና ስልጠና ሲሆን አስተማሪዎቹም ሆነ የዲፓርትመንት ሓላፊ ኣዳዲስ ምሩቃን ነርሶች ናቸው፡፡ በዐለም ለመጀመርያ ጊዜ በነርሶች የሚማሩ ዶክተሮች የሚመረቱባት ሀገር- ኢትየጵያ፡፡

ቀጥሎ ደግሞ በዚች ሀገር የጤናው ዘርፍ ቀጥተኛና ከባድ ጉዳት ያደረሰውና እስከቅርብ ጊዜ የቀጠለው የተፋጠነ የጤና መኮንንነት (accelerated health officer ) ስልጠና ነው፡፡ ይኸው በዋናነት የፓርቲው ታማኝ ሰዎች በአንድ ዐመት ተኩል ስልጠና Health officer ተብለው የሚመረቁበትና ብዙዎቹም የሆስፒታሎች ስራ አስኪያጆች ሆነው የሚሾሙበት አሰራር ነው፡፡ መቸም ሳይማር ወረቀት ያገኘ ሰው የመማርና የልፋት ትርጉም አያውቅምና እነዚህ ሰዎች የከፍተኛ ባለሙያዎች ፀር በመሆን ተወዳዳሪ የሌላቸውና የሕክምና አሰጣጡን በከፍተኛ ደረጃ የጎዱ ናቸው፡፡

በርካታ ተመሳሳይ አብነቶች መጥራት ይቻላል፡፡

የዝቅጠቱና የድፍረቱ ቀጣይ ክፍል ደግሞ “ኢቦላን በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች እንቆጣጠረዋለን” የሚል እጅግ አሳፋሪ ንግግር ነው፡፡

ከአስረኛ ክፍል ወድቀው የስድስት ወር ትንሽ ስልጠና ያገኙ ክትባት ከመስጠት ውጪ ስለሕክምና ምንም ነገር ያልሰለጠኑ፣ ምንም የማያውቁ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንዴት ይህንን ዐለምን ያስጨነቀና መድሓኒት ያልተገኘለት ቀሳፊ በሽታ “ይቆጣሩታል” ተብሎ ሰው ፊት ይወራል? ሲቀጥልም “ባለፉት ስድስት ዐመታት ጠንካራ የprimary health care ሲስተም ተሰርቷል” ይላል፡፡ እሱ የራሱን ስራ እና እያዋደደ ያለው፡፡በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ፡፡
የትኛውም የሕክምና ባለሙያ በተለይም ሓኪም አሁን ያለው የታይታ የጤና ፖሊሲና አሰራር እጅግ የሾቀ እንደሆነና ለስራ እንቅፋት እንደሆነ ይነግራችኃል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ግን ለልፋታቸው ክብር የሚገባቸው ቢሆኑም እውነታው እንኳን ኢቦላ ወባና የሳምባ ምች የሚያክሙበት በቂ ስልጠና የላቸውም፡፡ አሁን እንደአዲስ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ ያለው የmeasles በሽታም በዋናነት ክትባቶቹን በስነ-ስርዐት ባለመያዝ (cold chain ባለመጠበቅ)ና፣ በተገቢው ባለመስጠታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠየቁበት እነሱ ሳይሆኑ በቂ ስልጠናና እውቀት ያላስጨበጣቸው አካል ነው፡፡ እነሱ በትንሽ ገንዘብ ታች ወርደው እየሰሩና መከራቸውን እየበሉ ያሉ ናቸው፡ ቢሆንም ግን ከመነሻውም በዋናነት ለፕሮፖጋንዳ ታስቦ የተሰራ ነውና ምንም ተጨባጭ መሰረታዊ ስልጠናና እውቀት አንዲጨብጡ አይደረጉም፡፡

ያም ሆነ ይህ ያለሙያውና ከንቀት የመነጨ አባባሉ እጅግ የሚያስቆጣ የድፍረትና የድንቁርና ንግግር ነውና እናወግዘዋለን፡፡ ኢቦላ እንዳይገባ መከላከልና መከልከል እንጂ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ እንኳን እኛን በደምብ የተደራጀ የጤና መሰረተ-ልማትና ቅንጅታዊ አሰራር ያለው የዳበረ የጤና ሲስተም ያላቸውን አውሮፓንና አሜሪካን እንኳ ከፍተኛ ስጋት የደቀነባቸው ከባድ አደጋ ነው፡፡ በሆነ ምክንያት ሀገራችን ቢገባ ግን በዚህ የሾቀ የጤና መሰረተ-ልማትና የወረደ የጤና ፖሊሲ ቅንጅት ለመቆጣጠር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ድንቁርና ወለድ ድፍረት ቢቀርብንስ?
ኢቦላ እንዳይገባብን መከላከል ነው ብቸኛው አማራጭ-ጃል፡፡


No comments:

Post a Comment