Friday, November 14, 2014

የሶዶ ከተማ ጎዳና ተዳዳሪዎች በግዳጅ ካምፕ እንዲገቡ ተደረገ

ከህዳር 6/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 10/2007 ዓ.ም በሶዶ ከተማ የሚደረገውን የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባዔ አስመልክቶ ሶዶ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎች በግዳጅ ወደ ካምፕ እንዲገቡ መደረጋቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡

በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሴት፣ አዛውንትና ህጻናት ጎዳና ተዳዳሪዎች ሶዶ ውስጥ አራዳ ክፍለ ከተማ ተብሎ በሚጠራውና አዲስ እየተሰራ በሚገኘው ገለሜ የተባለ እስር ቤት ውስጥ በግዳጅ እንዲገቡ መደረጉን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ካምፕ ውስጥ የገቡትን የጎዳና ተዳዳሪዎችም የቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ለሳምንት ቀለብ እንደሚያቀርብላቸውና ጉባዔው ካለቀ በኋላ ወደነበሩበት እንደሚመለሱም ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ለጉባኤው ሲባል ዜጎችን በግዳጅ ወደ ካምፕ ማስገባቱ ደኢህዴን በከተማዋ ልማት እንደተመዘገበና ህዝቡን ከድህነት እንዳላቀቀ ለማስመሰል ያደረገው አስነዋሪ ተግባር ነው›› ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ የወላይታ ዞን የአደረጃጀት ኃላፊ አቶ ታደመ ፈቃዱ ‹‹እስካሁን ሶዶ ከተማ ውስጥ መብራት ስለማይኖር በርካቶች ተዘርፈዋል፡፡ የተገደሉም አሉ፡፡ የከተማዋ ውበትም እምብዛም የተጠበቀ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ከተማዋን ለማጽዳት እየተሯሯጡ ነው፡፡ መብራት ባልነበረበት ከተማ መንገዱ ሁሉ ባውዛ ሆኗል›› ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል፡፡

ለደኢህአዴን ጉባዔ ተብሎ የከተማዋ ውበት እንዲጠበቅና የጠፉት አገልግሎቶች ለጊዜው እንዲስተካከሉ መደረጉም በህዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል ተብሏል፡፡ ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው አንድ የከተማዋ ነዋሪም ‹‹ህዝቡ በአገልግሎቶች መጥፋት ተማሯል፡፡ የከተማው ውበት ለሚኒስትሮቹ እንጅ ለእኛ አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደኢህዴን በየ15 ቀኑ ጉባዔ ቢያደርግ ጥሩ ነበር›› ሲሉ ስለሁኔታው ገልጸውልናል፡፡

ለጉባዔው ሲባልም በጸጥታ ስም በተቃዋሚዎች ላይ ክትትል እየተጠናከረ ይገኛል ያሉት አቶ ታደመ ‹‹ከተማዋ በፖሊስ ተጥለቅልቃለች፡፡ ፖሊሶች በየ 10 ሜትሩ ቆመው ነው የሚታዩት፡፡›› ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment