በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው አራቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ በሚገኙበት የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስሩም ተከሳሾች ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ ተከሳሾቹ ህገ መንግስቱን በመጥቀስ ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የጸረ ሽብር አዋጁን በመጥቀስ ዋስትናው እንዳይፈቀድ ያቀረበውን መከራከሪያ በመቀበል የዋስትና ጥያቄውን አልተቀበለውም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ክሱን መርምሮ በሂደት ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠበቆች የቀረበውን ማስረጃ አለመሟላት በመመርመር አቃቤ ህግ ለህዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማስረጃዎችን አሟልቶ እንዲቀርብ በሚል አጭር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው ዕለት ተከሳሾች ከላይ ሙሉ ነጭ ሸሚዝ ለብሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ነጭ ማድረጋቸውም ‹ሰላማዊ ነን› የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ በማለም እንደሆነ መረዳት ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment