Tuesday, November 4, 2014
ጦማርያንና ጋዜጠኞቹ ለሳምንት ቀጠሮ ተሰጠባቸው
ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለ10ኛ ጊዜ ችሎት የቀረቡት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሶስቱ ጋዜጠኞች ለሳምንት (ህዳር 3/2007 ዓ.ም) ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በጦማርያንና በጋዜጠኞቹ ቀደም ሲል የቀረበውን የክስ ማሻሻያ አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ምርመራው አላለቀም በሚል ምክንያት አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው ችሎት ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ አዲሶች በመሆናቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃ አምሃ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ዳኞች ብቻ ሳይሆን ችሎት ክፍሉም በመቀየሩ ክፍሉ ጠባብ ነው በሚል፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ችሎት መግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከሳሾች ዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አቶ አምሃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በተከሳሾች በኩል ደግሞ፣ ሁለቱ ሴት ተከሳሾች (ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን) በቃሊቲ ማረሚያ ላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት አቤቱታ በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ ድጋሚ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ስማቸው ቀድሞ በተመዘገቡ ሰዎች ብቻ እየተጎበኙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment