ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሰብዓዊ መብቶች አካባቢ ላይ ልዩ የመወያያ መድረክ እንዲያዘጋጅ አሜሪካ ጠየቀች።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለበርካታ ሃገራት አለመረጋጋት ምክንያት እየሆኑ መምጣቱን የገለጸችው አሜሪካ፣ ምክር ቤቱ የሰብዓዊ መብት መከበር ግጭትን ለመከላከልና ለአለም ሰላምና ደህንነት ያለው ሚና ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስባለች።
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኒኪ ሃሊ ቀጣዩ የአለም ቀውስና አለመረጋጋት የሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩባቸው ሃገራት ላይ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ገልጸዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቁት አምባሳደሯ፣ የብሩንዲንና የማይንማር መንግስታትን በምሳሌነት በመጥቀስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚስተዋልባቸው ሃገራት መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያና ሶሪያ በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው የተቹት አምባሳደር ኒኪ የጸጥታው ምክር ቤት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በቂ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱን አውስተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በአግባቡ የማይከታተልና ልዩ ትኩረትን የማይሰጥ ከሆነ ድርጊቱ ለአለም የጸጥታና ደህንነት ስጋት ይሆናል ሲሉ አምባሳደሯ አሳስበዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው አሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች መከበር በጸጥታው ምክር ቤት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያቀረበችው ጥያቄ ችግር ላለባቸው ሃገራት መልዕክትን ያስተላለፊ እንደሆነ ገልጸዋል። በተያዘው ወር የምክር ቤቱን በፕሬዚደንት የምትመራው አሜሪካ ማክሰኞ ለመጀመሪያ ጊዜ የጸጥታው ምክር ቤት ትኩረቱን በሰብዓዊ መብት ላይ አተኩሮ እንዲያካሄድ ማደረጓን ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።
ይሁንና የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካ እየወሰደችው ያለው ዕርምጃ የምክር ቤቱን ሃላፊነት የዘለለና የድርጅቱን አሰራር የጣሰ ድርጊት ነው ሲሉ ተቃውሞን አቅርበዋል።
የግብፅ የሩሲያ፣ እንዲሁም የቦሊቪያ ተወካዮች የአሜሪካ ሃሳብ በአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳት ጣልቃ የመግባት አካሄድን ያመጣል በማለት ቅሬታን ሰንዝረዋል።
አለም አቀፍ ድርጅቶች የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሰብዓዊ መብት አከባበር ዙሪያ ጠንካራ አቅጣጫን ለመከተል ከወሰነ የሃገሪቱ አጋር የሚባሉ ሃገራት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቀድሞ የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በሽብርተኛ ዘመቻ ላይ አጋር አድርጎ የያዛቸው ሃገራት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ በዝምታ ተመልክቷል የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል።
ይኸው የአሜሪካ አካሄድ በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ ጥያቄን አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment