ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ሃገሪቱ ልማት ባንክ በብድር ስም እየተራቆተ መሆኑን ምንጮች ገለጹ። ለባንኩ ፕሬዚደንት በጉቦ መልክ እጅግ ዘመናዊ ቤት የተሰራላቸው ቢሆንም፣ እርሳቸው የሚኖሩበት ግን ባንኩ በዋስትና በወረሰው ቤት ውስጥ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የህወሃት ንብረት ለሆነው ኤፈርት ኩባንያዎች ብድር ምንጭነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሃብቶችም ከህግና ደንብ ውጭ ከፍተኛ ገንዘብ እየወሰዱ ሲሆን፣ የአንዳንዶቹ ብድር ከ2 ቢሊዮን ብር መብለጡንም ለኢሳት በዝርዝር የደረሰው መረጃ ያስረዳል።
በዚሁ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዱ የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ መሆናቸውም ተመልክቷል። ባለሃብቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትና ያልተመለሰው ብድር 1.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም፣ ዕዳቸውን ሳይከፍሉ ያለጨረታ ግዙፍ የባንኩን ፕሮጄክቶች እየወሰዱ ይገኛል።
መገናኛ አደባባይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንጻ ያለጨረታ መስራታቸውን የሚገልፁት የባንኩ ምንጮች፣ ባንኩ ልደታ አካባቢ የሚያሰራውንም ህንጻ በተለየ ሁኔታ ያለጨረታ እንዲወስዱ መደረጉም ተመልክቷል። ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት ተገልሎ ግንባታው ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽ የተሰጠበት ሁኔታ በግልፅ አልተመለከተም።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት አመራሮች እንዲሁም ቀደምት ታጋዮችና የጦር አዛጆች በይበልጥም ከአቶ አባይ ጸሃዬና ከብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር በቅርበትና በሽርክና ይሰራሉ የሚባሉት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ፣ በአቶ አባይ ጸሃዬ ትዕዛዝ ይንቀሳቀሳሉ ለሚባሉት የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ገንብተው በስጦታ መስጠታቸውን መረዳት ተችሏል።
አቶ በቃሉ ዘለቀ በስጦታ የተበረከተላቸው ቤት በዋስትና አስይዘው ራሳቸው ብድር እንደወሰዱ የሚገልጹት ምንጮች፣ አዲሱን ቤት አከራይተው ባንኩ በዋስትና በወረሰው ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸዋል። ባንኩ በ10 ሚሊዮን ብድር በዋስትና ይዞ የወረሰውን ቤት ባንኩ ሽጦ ገቢ ማድረግ ሲገባው፣ የባንኩ ፕሬዚደንት እንዲኖሩበት መደረጉ ጥያቄ ማስነሳቱን መረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነትን በአሁኑ ወቅት የያዙት አቶ በረከት ስምዖን ቢሆኑም፣ በእያንዳንዱ የባንኩ እንቅስቃሴ የባንኩን ፕሬዚደንት አቶ በቃሉ ዘለቀን እየተቆጣጠሩ የፈቀዱትን የሚያስፈጽሙት የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አባይ ጸሃዬ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ አባይ ጸሃዬ አሁን የቦርድ ሊቀመንበርነቱን ቢለቁም፣ የቦርድ አባል መሆናቸው ታውቋል።
No comments:
Post a Comment