ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2009)
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኘውን የአህያ ቄራ ለመዝጋት የወሰደውን ዕርምጃ በመቃወም የቻይናውን ኩባንያ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ማክሰኞ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፋብሪካው መዘጋትን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የአህያ ማረጃ ቄራው እንዲዘጋ መወሰኑ ተገልጿል።
ይሁንና የከተማው የአስተዳደር ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም የቄራው ባለቤት የሆነው የቻይናው ሻንዶንግ ዶንግ ኩባንያ ጉዳዩን ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እያጤነ መሆኑን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ የኩባንያውን ምንጮች ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር እንዲዘጋ የተወሰነው የአህያ ቄራው በየዕለቱ 200 አህዮችን ለእርድ በማቅረብ ስጋን ወደ ቬይትናም እንዲሁም የአህያ ቆዳን ደግሞ ወደ ቻይና ለመላክ እቅድ ይዞ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱ ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ጋር የሚጻረር ነው በማለት በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች ከተሰጠው ፈቃድ ውጭ ፈቃዱ ከእንግዲህ በኋላ አይሰጥም ሲል ምላሹን መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና ኮሚሽኑ በቢሾፍቱ እና በአሰላ ከተማ የተቋቋሙት የአህያ ማረጃ ቄራዎች ፈቃዳቸው ይሰረዝ አይሰረዝ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።
ኮሚሽኑ ድርጊቱ ከሃገሪቱ ባህልና እሴት ጋር የሚጻረር ነው ቢልም በቀጣይ የሚሰጥ ተመሳሳይ ፈቃድ አይኖርም ማለቱ የሚታወስ ነው። የቻይና ኩባንያ ጉዳዩን ለየትኛውም አለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ የታወቀ ነገር የለም።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር እንዲዘጋ የተወሰነው የአህያ ማረጃ ቄራው ለሙከራ ባካሄደው ስራ ከ300 በላይ አህዮችን ለእርድ ማዋሉን ለመረዳት ተችሏል።
የቻይና ኩባንያዎች በተመሳሳይ መልኩ በቡርኪና ፋሶ፣ ናይጀሪያና ሌሎች ሃገራት ያቋቋሟቸው የአህያ ቄራዎች ተቃውሞ ቀርቦባቸው እንዲዘጉ መደረጋቸውን ከተለያዩ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment