ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2009)
በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተጨማሪ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው መውታጣቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ቁጥራቸው ያልተገለጸው ወታደሮቹ በማዕከላዊ ሶማሊያ ከሚገኘውና ኤልቡር ተብሎ ከሚጠራ አስተዳደር ለቆ መውጣቱን የአካባቢው የክልል ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥረው ከቆዩት አስተዳደር በምን ምክንያት ለቀው እንደወጡ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ኤልቡርን እንደተቆጣጠረ ቪኦኤ የእንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።
የኤልቡር አስተዳደር ሃላፊ የሆኑት ኑር ሃሰን ጉታሌ የኢትዮጵያ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው እንደሚወጡ አስቀድመው የሰጡት መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።
የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት የሆነው አልሸባብ ሰኞ ማለዳ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በመታጀብ ያለምንም ግጭት አስተዳደሩን ሊቆጣጠር እንደቻሉ ጉታሌ አክለው አስረድተዋል።
ፀረ-አውሮፕላን መሳሪያዎችን ጭምር የታጣቁት አልሸባብ ተዋጊዎች ከስድስት በሚበልጡ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማው ከገቡ በኋላ በትላልቅ ህንጻዎች ላይ የራሳቸውን ባንዲራ እንደሰቀሉም ነዋሪዎች ለዜና ወኩሉ ተናግረዋል።
የአስተዳደር ሃላፊ የሆኑት ኑር ሁሴን ቱጋሌ የኢትዮጵያ ወታደሮችና የታጣቂ ቡድኑ አባላት በነዋሪዎች ላይ እንግልት መፈጸማቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች በታጣቂ ሃይሉ ቁጥጥር ስር የወደቀችውን አስተዳደር ላለፉት ሶስት አመታት ተቆጣጥሮ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።
በርካታ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ወታደሮች ግዛቲቱን በተቆጣጠሩ ጊዜ ለቀው እንደወጡ ያወሱት ሃላፊው የተቀሩት ሰላማዊ ሰዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች እንግልት ሲደርስባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ከአራት ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ጠቅለው መውጣታቸው ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናት ዕርምጃው ስልታዊ እንደሆነ በመግለፅ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሶማሊያ መንግስትን ለማጠናከር የወሰዱት ዕርምጃ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል ሲሉ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም። ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ወታደሮቿን ከሶማሊያ በማስወጣት ላይ ብትሆንም አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአል-ሸባብ ላይ የአየር ጥቃትን ያካተተ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚወሰድ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዕሁድ ወታደሮቹን ከኤል-ቡር ለማስወጣት የወሰደው ዕርምጃ አሜሪካ አዲስ ስልት በሃገሪቱ ላይ ለመከተል የወሰነችውን ውሳኔ ተከትሎ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች አስረድተዋል።
ይሁንና የትራምፕ አስተዳደር በሶማሊያ ለመከተል የወሰነው አዲስ አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን እንደበፊቱ ያሳተፈ ይሁን አይሁን እስካሁን ድረስ የተሰጠ ፍንጭ አለመኖሩም ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment