ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ሁለት ባልደርቦች ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰማሩ ጊዜ ከ380 ሺ ብር በላይ ከተጠርጣሪ ወስደዋል ተብለው ክስ ተመሰረተባቸው።
አቶ ባህሩ አዱኛና አቶ ደራ ደስታ የተባሉ የደህንነት ሰራተኞቹ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ነዋሪ የሆኑትን አቶ ኡመር አብዶ የተባሉ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰማሩ ጊዜ 418 ሺ 500 ብር መያዛቸውን ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ ማቅረቡን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። ይሁንና የደህንነት ሰራተኞቹ የወሰዱትን ገንዘብ ሳያስመዝግቡ 30ሺ ብር ብቻ በኤግዚቢትነት ማስመዝገባቸው ተመልክቷል።
የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሁለቱ የደህንነት ሰራተኞች ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ወንጀልና በስራ ተግባር ላይ የሚፈፅም የመውሰድና የመሰወር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል።
ተከሳሾቹ ክስ ከተሰጣቸው በኋላ ጠበቃ ለማቆም አቅም እንደሌላቸው ለፍርድ ቤት በመናገራቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ተከላካይ ጠበቅ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ አስተላልፏል። ክስ የመስማቱ ሂደትም ሚያዚያ 25 ቀን 2009 አም እንደሚሰጥ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment