ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚኖሩ 10ሺ ነዋሪዎች ለመልሶ ልማት ከመኖሪያ ቀያቸው ሊነሱ መሆኑ ተገለጸ።
ከተቆረቆረ ረጅም ጊዜ እንደሆነ በሚነገርለት በዚሁ አካባቢ በርካታ በቅርስነት መፍረስ የሌለባቸው ህንጻዎች ያሉ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና የታሪክ ምሁራን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
አካባቢውን በቀጣዮቹ ስድስት ወራቶች ሙሉ ለሙሉ ለማፍረስ ሃላፊነት የተሰጠው የአራዳ ክፍለ ከተማ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጨምሮ 14 ቤቶች በቅርስነት በመታየታቸው እንደማይፈርሱ አስታውቋል።
ይሁንና የከተማ ነዋሪዎች አካባቢው ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ በመሆኑን ከ14 በላይ የሚሆኑ ይዞታዎች በቅርስነት መያዝ እንደሚኖርባቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በሰራተኛ ሰፈር በወረዳ 10 ቀበሌ 10 እና 13 ዙሪያ ያሉ 1ሺ 600 መኖሪያ ቤቶች በተያዘው አመት መጨረሻ ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንደሚፈርሱና በድርጊቱ ወደ 10 ሺ አካባቢ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንደሚነሱ ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ስር ያሉ ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ አካላት ይዞታ ስር የነበሩ በርካታ የንግድ ተቋማት በመልሶ ማልማት ሂደቱ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ እንደሚያደርግ ለመረዳት ተችሏል።
አካባቢውን የማፍረስ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ የከተማዋ አስተዳደር ሰፊ ቦታውን በሊዝ ጨረታ ለአልሚዎች ለመሸጥ እቅድን የያዘ ሲሆን፣ ከመሬት ሽያጩ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚሰበሰብ ተመልክቷል።
በክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ሃላፊ የሆኑት አቶ ዮሃንስ አድማሱ ነዋሪዎቹን ለማንሳት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ሲሉ ለጋዜጣው አስረድተዋል።
ከ1ሺ በላይ በሚሆኑ የቀበሌ ቤት ይዞታ ውስጥ የሚገኙ ተነሺ ነዋሪዎች አቅማቸው የሚፈቅድ ከሆነ የኮንዶሚኒየም ቤት በአማራጭነት እንደሚቀርብላቸውና አቅም የሌላቸው ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች በቀበሌ ቤት እንዲገቡ እንደሚደረግ የአራዳ ክፍለ ከተማ አስታውቋል።
በግል ይዞታ ስር ላሉ 260 አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ ምትክ ቦታና ካሳ እንደሚሰጣቸው አቶ ዮሃንስ ገልጸዋል። ይሁንና ሃላፊው ለግል ይዞታ ላላቸው ተነሺዎች የሚሰጣቸውን የመሬት እና የካሳ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የያዘው እቅድ አለመሳካቱን ተከትሎ ከአልሚዎች ለሚቀርብለት የመሬት ጥያቄ ፊቱን በመዲናይቱ ማደረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
አስተዳደሩ በተያዘው እና በቀጣዩ አመት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በርካታ ነዋሪዎችን በልማት ስም በማንሳት መሬትን ለባለሃብቶች በሊዝ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑ ታውቋል።
ይሁንና ከተያያዙ አካባቢዎች በመነሳት ላይ ያሉ ተነሺዎች መሰረተ ልማት ወዳደ አልተማላለት ቦታ እንዲሄዱ መደረጉን ሲቃወሙ ቆይተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከግል ይዞታ የተነሱ ነዋሪዎች የሚሰጣቸው ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ በጣም አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment