ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2009)
በኦሮሚያክ አማራና የደቡብ ክልሎች ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 669 ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማክሰኞ ገለጸ።
በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ምርመራ አስመልክቶ ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀረበው ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በቢሾቱ ከተማ ከእሬቻ በዓል አከባባር ጋር በተገናኘ የደረሰውን የሞት አደጋ ጨምሮ በተለያዩ ዞኖች የተፈጸሙ ግድያዎችን አቅርቧል።
በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖች እና 91 ከተሞች በአማራ ክልል 5 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌድዮ ዞን በሚገኙ ስድስት ከተሞች ምርመራው መካሄዱን የኮሚሽኑ ሃላፊ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚያብሄር ለፓርላማው አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል 462 ሰላማዊ ሰዎችና 33 የጸጥታ ሃይሎች ተገድለዋል ያለው የኮሚሽኑ ሪፖርት በአማራ ክልል 110 ሰላማዊ ሰዎችና 30 የጸጥታ አባላት መሞታቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በደቡብ ክልል የ34 ሰዎች ህይወት ማለፉን ያወሳው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በባሌ ሮቤና በምስራቅ ሃረርጌ 28 ሰዎች የሞቱበት እንዲሁም በዳዳሴ ከተማ የተካሄደው የጸጥታ ሃይሉ ዕርምጃ የተመጣጠነ አለመሆኑን አመልክቷል።
የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የእሬቻን በዓል በሚከበርበት ወቅት ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል በቂ መረጃ እያላቸው ጥንቃቄና በቂ ጥበቃ አለማድረጋቸው ሃላፊነት የጎደለው ነው ሲል ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስፍሯል።
የጸጥታ ሃይሎች በበዓሉ ማግስት የነበረውን ብጥብጥ ባለመቆጣጠሩ ሊጠየቅ ይገባዋል ያለው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጸጥታ አባላት በበአሉ ወቅት ያሳዩት ትዕግስት የሚመሰገን ነው ብሏል።
የአይን እማኞችና በወቅቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ ዕርምጃ መውሰዳቸውን ቢያረጋግጡም ኮሚሽኑ በወቅቱ ከአስለቃሽ ጭስ ውጭ የተወሰደ የሃይል እርምጃ የለም ብሏል።
የመንግስት ባለስልጣናት በወቅቱ ከ50 በላይ ሰዎች ሞተዋል ቢሉም መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምን ያህል ሰው እንደሞተ የሰጠው መረጃ አለመኖሩን ለመረዳት ተችሏል።
ሃምሌ 18 ፥ 2008 አም በጎንደር ማራኪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተወሰደው ዕርምጃ ህጋዊና ተመጣጣኝ መሆኑን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል። ይሁንና በደምቢያ መንገድ በዘጉና፣ በደባርቅ፣ በወገራ፣ በደብረታቦር መኪና ላይ ድንጋይ የወረወሩ ግለሰቦች እንዲሁም በስማዳ፣ በእብናት፣ በወረታ እና በዳንግላ የጸጥታ ሃይሉ አላስፈላጊ የሃይል እርምጃ መውሰዱ ተመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል የመልካም አስተዳደር ችግር የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ህገመንግስቱ በሚደነግገው መሰረት ተግባራዊ አለመደረግ እንዲሁም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለህዝባዊ አመጹ ምክንያት ናቸው ተብለው ቀርበዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በአማራ ክልል የወልቃይት የማንነት ጥያቄ፣ የትግራይ የበላይነት አለ የሚሉ ቅሬታዎች፣ የዳሽን ተራራ በመማሪያ መጽሃፉ ውስጥ በትግራይ ክልል ስር እንዲካተት መደረጉ፣ የአማራ ክልል መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚሉ ጉዳዮች ለሁከት መንስዔ ነበሩ ሲል ኮሚሽኑ ለሪፖርቱ አመልክቷል።
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ለተከሰተው ብጥብጥ የመልካም አስተዳደር እጦት እና ኢፍትኣዊ ተጠቃሚነት ምክንያት ናቸው ተብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ የጸጥታ ሃይሉ በአብዛኛው ስፍራዎች ተመጣጣኝ እርምጃን ወስዷል በማለት ለፓርላማው ገልጿል።
No comments:
Post a Comment