ኢሳት (ሃምሌ 27 ፥ 2008)
ከውጭ ብድር በማግኘት ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ ግንባታው እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ለስራው ማስኬጃ የሚሆን ብድር አለመገኘቱ ተገለጸ።
ለፕሮጄክቱ ማስኬጃ የሚሆነው 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ብድር እንዲያፈላልግና ግንባታውን እንዲያከናውን ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ መንግስት በሚፈልገው የወለድ ምጣኔ ብድር ማግኘት አለመቻሉን አስታውቋል።
ለፕሮጄክቱ ማስኬጃ የሚሆነው 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ብድር እንዲያፈላልግና ግንባታውን እንዲያከናውን ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ መንግስት በሚፈልገው የወለድ ምጣኔ ብድር ማግኘት አለመቻሉን አስታውቋል።
ኩባንያው ብድሩን ማግኘት ቢችልም የብድሩ ወለድ መንግስት ለብድር ካስቀመጣቸው መስፈርቶች ጋር አይመጣጠንም ሲል ለሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ መስጠቱ ከሀገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ላገኘው ብድር የተጠየቀውን የወለድ መጠን ያልገለፀ ሲሆን፣ መንግስት ፕሮጄክቱን ፋይናንስ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።
ይሁንና መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል ለተባለው ፕሮጄክት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ በብድር እጦት ምክንያት የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ሊዘገይ ይቻላል ተብሎ ተሰግቷል።
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ ይገነባል ተብሎ የታቀደው ይኸው ፕሮጄክት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ተካቶ የሚገኝ ሲሆን፣ 2ሺ 200 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሶስቱን የግልገል ጊቤ ወንዝ የሃይል ማመንጫዎች እና የጣና በለስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ የገነባና በመገንባት ላይ ያለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የአባይ ግድብ ግንባታን እያከናወነ ይገኛል።
ኩባንያው ብድር አለማግኘቱን አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁ የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው አመት አለም አቀፍ ገበያ ካቀረበው የቦንድ ሽያጭ ያገኘውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ለሃይል ማመንጫ ግንባታ እንዲውል ያደረገ ሲሆን፣ ገንዘቡ ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በወቅቱ ገልጸዋል።
ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ የእዳ ክምችት እንዳለባትና የወለድ መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።
No comments:
Post a Comment