ኢሳት (ሃምሌ 29 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ሊካሄድ ሊካሄድ የታቀደውን የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ ተቃውሞ በተለያዩ መንገዶች በማስተባበር ላይ የሚገኙ አካላት ህዝባዊ ተቃውሞ በተያዘለት ቀንና ፕሮግራም እንደሚካሄድ ለኢሳት ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ አካላት የተቃውሞ ሰልፍን ለማድመቅ የሚረዱ የተለያዩ ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን እና ህዝቡ ያለውን ጥያቄ ለማሰማት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አርብ በቴለቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ ሊካሄድ የታሰበው የተቃውሞ ሰልፍ ህገወጥ መሆኑን እና መንግስት እርምጃን እንደሚወስን ማሳሰባቸው ታውቋል።
ይሁንና በተለያዩ መንገዶች ቅስቀሳን እያደረጉ ያሉ አስተባባሪዎች ቅዳሜ በሚካሄደው ሰልፍ በህዝብ ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ትኩረት እንደሚያገኙ ለኢሳት አስታውቀዋል።
ለወራት በክልሉ ከዘለቀው ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጥያቄን እንደሚቀርብ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተለያዩ የምስራቅ አርሲ እና ምዕራብ ሃረርጌ ባሉ ዞኖችም ዳግም መቀስቀሱ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment