ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከፍተኛ ሕመም በስቃይ ላይ የሚገኘውና በ አገር ውስጥ ታክሞ መዳን እንደማይችል በሕክምና ቦርድ የተፈረመ ማረጋገጫ የተሰጠው አቶ ሃብታሙ አያሌው የተንዛዛ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠው ሕይወቱ አደጋ ላይ ይገኛል። በዛሬው እለት የሀብታሙ አያሌው የሕክምና ጉዳይ ላይ የአቃቤ ሕግን አስተያየት ለመቀበል የተሰየመው ችሎት አቃቤ ሕግ አስተያየቱን በቃል ሊያቀርብ ፈቃደኛ ቢሆንም ችሎቱ በጽሁፍ እንዲቀርብለት ለሀምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
”የአቶ ሀብታሙ በቶሎ ወደ ውጭ ሄዶ አስፈላጊው ህክምና ካላገኘ በሸታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሰው ዶክተሩ የፃፈለት እና ፍርድ ቤቱ በጠየቀው መሰረት የሆስፒታሉ ቦርድ 3 ዶክተሮች የፈረሙበት ወረቀት ቢቀርብም ጉዳዩ ምንም ተስፋ ወደሌለው ወደ ዳግም ቀጠሮ መዘዋወሩ አገዛዙ አቶ ሐብታሙ ላይ የሞት ፍርድ እንደፈረደበት እና ቀኑን እየቆጠረለት መሆኑን መቀበል ግድ እየሆነብን መጥቷል።” ሲሉ የአቶ ሀብታሙ ባልደረባና ጓደኛ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።
ጊዜያዊ ማደንዘዣ እየተሰጠው የአልጋ ቁራኛ የሆነው የቀድሞው የአንድነት ከፍተኛ አመራር የነበረው አቶ ሃብታሙ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትሕ ስም የሚፈጸመውን በደል በማህበራዊ ድረገጾች አውግዘዋል።
No comments:
Post a Comment