ኢሳት (ሃምሌ 27 ፥ 2008)
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ በመዲናይቱ በመሰራጨት ላይ ያለውን የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ መቆጣጠር አለመቻሉንና ተጨማሪ በርካታ ሰዎች በየዕለቱ በበሽታው በመያዝ ላይ መሆናቸውን ይፋ አደረገ።
የኮሌራ በሽታው ስርጭት ከተጠበቀው በላይ መሆኑን ተከትሎ የከተማዋ ጤና ቢሮ በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በዘመቻ ጀምሯል።
የኮሌራ በሽታው ስርጭት ከተጠበቀው በላይ መሆኑን ተከትሎ የከተማዋ ጤና ቢሮ በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በዘመቻ ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አድማሱ የመዲናይቱ ነዋሪዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ሳቢያ የበሽታው ስርጭት በመባባስ ላይ መሆኑን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው በከተማዋ ያለው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር ለበሽታው ስርጭት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የከተማዋ ነዋሪዎች የተበከሉ ወንዞች ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች በመጠቀማቸው የኮሌራ በሽታው ስርጭት ሊቀንስ አለመቻሉን አመልክቷል።
የፌዴራልና የከተማዋ ባለስልጣናት ለበሽታው ስርጭት የተለያዩ ምክንያቶች በመስጠት ላይ ቢሆኑም የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት (ኮሌራ) በሽታ ስርጭቱ የከተማዋ ዋነኛ የጤና ችግር መሆኑ ተገልጿል።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ጥረትን እያደረገ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ በርካታ ስራዎች ተግባራዊ ቢደረጉም አሁንም ድረስ በሽታውን መቆጣጠር እንዳልተቻለ አረጋግጧል።
የበሽታው አሳሳቢነትን በመረዳት በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከክፍለከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ የቤት ለቤት ትምህርት በዘመቻ መልክ በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጿል።
የከተማዋ ጤና ቢሮ የኮሌራ በሽታ ስርጭት እያደረሰ ያለውን አጠቃላይ ጉዳት መግለጽ በህብረተሰቡ ላይ ድንጋጤን ይፈጥራል በሚል መረጃን ይፋ ከማድረግ የተቆጠበ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች በበሽታው ምክንያት በሞት ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ባለፈው ወር በትንሹ ስድስት ሰዎች በዚሁ በሽታ እንደሞቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment