ኢሳት (ሃምሌ 29 ፥ 2008)
አርብ በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ የጀመሩትን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በከተማ መጠነ ሰፊ ግጭት በመካሄድ ላይ መሆኑን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።
የከተማዋ ነዋሪዎች አርብ ረፋድ የወልቃይት ጠገዴ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ መባሉን ተከትሎ ለተቃውሞ ፍርድ ቤት ቢሰባሰቡም ድርጊቱ ወደ ግጭት መለወጡ ታውቋል።
ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደጎንደር ከተማ የሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች መዘጋታቸውን የተናገሩት እማኞች አርብ ረፋድ ድረስ በተወሰደ የተኩስ እርምጃ በትንሹ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ለመረዳት ተችሏል።
ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት የኮሚቴ አባሉ ፍርድ ቤት ባይቀርቡም ፍርድ ቤት አካባቢ የተሰባሰቡ የከተማ ነዋሪዎች በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የተቃውሞ ድምፅ በማሰማት መጀመራቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከኢሳት ጋርይ ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከቀናት በፊት የወልቃይት ጉዳት የህዝብ ጥያቄ አይደለም ሲሉ ምላሽን ቢሰጡም ከሁለተኛ ጊዜ ህዝባዊ ተቃውሞን የጀመሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በባለስልጣናት የተሰጠው ምላሽ እንዳስቆጣቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይሁንና ህዝቡ ማሰማት የጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ እርምጃን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ፣ የጎንደር ከተማ አርብ ማምሻውን ድረስ በተኩስ ሩምታ ውስጥ መሆናቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
የባለስልጣናት ስሞችን በማንሳት የተቃውሞ ድምፅን ሲያሰሙ ያረፈዱት ሰልፈኞች ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ራሳቸውን በማደራጀት መጠነ ሰፊ ተቃውሞ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን በአስለቃሽ ጭስ እና በጥይት የተኩስ ድምፅ ታጅበው ሁኔታውን ለኢሳት ያስረዱ እማኞች አስታውቀዋል።
በፍርድ ቤት አካባቢ የተጀመረውን ይህንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ በሰዓታት ልዩነት በርካታ ህዝብ በመቀላቀል ተቃውሞ በመላው ከተማ መዳረሱ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment