Friday, August 5, 2016

“በህወሀት ሽብር፣ ትጥቁን አይፈታም ጎንደር” – በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የአርማጭሆ ተወላጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በዚህ ወር፣ በታሪካዊ መዲናችን በጎንደር ከተማ፣ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተፈጽመዋል። ሀምሌ 24፣ 2008 ዓም ጎንደር ላይ የታየው ታሪካዊ ሰላማዊ ሰልፍ አለምን አስደንቋል። ይህ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ የተሳተፈበት፣ በላቀ ስነምግባርና ቆራጥነት የተመራው ሰልፍ፣ የአማራውን ህዝብ ታላቅነትና ደግነት አስመስክሯል። በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ፣ ከመላው የአማራ ክልሎች የተሰባሰው ህዝብ፣ ለወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ በሚኖረው የአማራው ህዝብ ላይ ህወሀት የሚፈጽመውን የዘር ማጽዳት ዘመቻ በአንድ ድምጽ በማውገዝ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ እውነተኛ የዜጎችን እኩልነት የሚያስከብር፣ የሀገራችን ሉዓላዊነት የሚረጋግጥ፣ የእምነት ነጻነትን የሚንከባከብ ሥርዓት እንዲመሰረት በአንድ ድምጽ ጥሪ አድርጓል። ይህን አዲስ ትግል መዕራፍ የከፈተልን፣ ጀግናው የጎንደር ህዝብ፣ ህወሀት የከፈተበትን ጥቃት ለመከላከል ሀምሌ 5 ቀን፣ የፈጸመው ተጋድሎና የከፈለው መስዋዕትነት ነው። የጎንደር ህዝብ ጀግኖች ልጆቹን ገብሮ ያቀጣጠለው ትግል እንዲሳካ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በህብረት ልንነሳ ይገባል።


 እኛም በሰሜን አሜሪካ የምንገኛ የአርማጭሆ ተወላጆች፣ በጎንደር ጀግኖች መስዋዕትነት የተቀጣጠለው የነጻነት ፋና እውን እንዲሆን፣ ታሪካዊ ጥሪውን ተቀብለው፣ የነጻነት ልሳኑን አንግበን በአጋርነት የተነሳን መሆኑን በዚህ መግለጫ ይፋ እናደርጋለን። ሀምሌ 5፣ 2008 ዓ.ም የጎንደር ከተማ የተከሰተው ህዝባዊ አመጽ ታሪካዊ ነው። ይህ እለት፣ የህወሀት የሽብር ግብረኃይል በጎንደር ከተማ ህዝብ ላይ የሽብር ጥቃት የከፈተበት ቀን ነው። ህወሀት የዚህ አይነት ጸረ አማራ አፈና እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ላለፉት 30 ዓመታት በአማራው ማህበረሰብ ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። በአማራው ክልል የተሾሙ የብአዴን አመራሮች ህወሀት እንደፈጣሪ ስለሚመለከቱት የወያኔ አፋኞች በክልሉ ያለ ምንም ጠያቂ ሰርገው እየገቡ ሰላማዊ ኗሪዎችን እያፈነ ሲወስድ ህዝቡን መከላከል አልሞከሩም። ይህም ወያኔ የሾማቸውን የክልሉም ባለስልጣኖች ምን ያህል እንደሚንቃቸው በይፋ ያሳያል።

ህወሀት የከፈተው የሽብር አፈና ያነጣጠረው ሰላማዊ የአማራ ማንነት ጥያቄ አንስተው የሚንቀሳቀሱ የወልቃይት ጠገዴ ሽማግሌዎችን አፍኖ ለመውሰድ የታቀደጸረ አማራ፣ ጸረ ጎንደር የሽብር ዘመቻ ሲሆን፣ ጀግናው የጎንደር ህዝብ ግን ወገኖቼን አሳልፌ አልሰጥም ብሎ ህዝባዊ አመጽ አነሳ። የጎንደር ህዝብ ግን ተቆርቋሪ መንግስት የሌለለው መሆኑን በመረዳት፣ ከህዝብ አብራክ የተፈጠሩ ህዝባዊ አርበኛች፣ ከቆላና ከደጋ አሰባስበው፣ የወያኔን የሽብር ግብረኃይል ሰብረው በመግባት በህዝብና በንብረት ላይ ከባድ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ጥቃቱን አክሽፈውታል። ይህን የሽብር ጥቃት ለመከላከል በተካሄደው ህዝባዊ አመጽ ከወያኔ በኩል የዘመተው 21 የሽብር ግብረኃይል ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል።

ከወገን በኩል ደግሞ እነ ሰጠኝ ባብል፣ ሲሳይ ታከለና እንዲሁም ሌሎች አርበኞች መስዋዕትነት የከፈሉ ሲሆን የመቁሰል ጉዳት ደርሷል። እነዚህ ጀግኖች ወገኖቻችን፣ የወያኔን የመከፋፈል ኬላ በመስበር እጅ ለእጅ ተያይዘው ጎንደር ላይ በደማቸው ህያው ታሪክ ጽፈው አልፈዋል። የህወሀት / ኢህአዴግ መንግስት፣ በጎንደር ህዝብ ላይ በፈጸመው ወንጀል ተጸጽቶ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅና የቀረቡትን ጥያቄዎች ተቀብሎ እስረኞችን መፍታት ሲገባው፣ የተገላቢጦሽ ከሳሽ ሆኖ ብቅ ማለቱ አስገራሚ ሆኗል። ወንጀል የፈጸሙትን ነጻ አድርጎ፣ ሰላማዊ ኗሪዎችን፣ በሽብር ፈጣሪነትና በኤርትራ ወኪልነት በመክሰስ፣ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አታላይ ዛፌና በርካታ ወገኖቻችን መታሰራቸው መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም አማራውን ኅብረተሰብ ሊያስቆጣ ይገባል። ህወሀት፣ ለብዙ ዘመናት የሀገር ኩራት ሆኖ የኖረውን የአማራ ህዝብ፣ ተላላኪዎቹን በማሰማራት፣ በጎንደር አውራጃዎች “አማራ ነን”፣ “ትግሬ አይደለንም”፣ “ወይልቃይት አማራ ነው” ብላችኋል፣ እየተባሉ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የወልቃይት፣የጠገዴ፣ የሁመራ፣ የጠለምትና የዳንሻ ተወላጆች ከተወለዱበት ቦታቸው እየተፈናቀሉ በሀገራቸው ስደተኞች ሆነዋል። በሰላማዊ መንገድ የማንነት ጥያቄ አንስተው የሚንቀሳቀሱ የህዝብ ተወካዮችን አፍኖ ለመውሰድ ህወሀት የፈጸመው ህገ ወጥ መንግስታዊ ሽብር፣ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ሁሉን ኢትዮጵያውያን ሊያሳስብ ይገባል። ጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ብዙ የትግራይ ሰዎች የተወለዱበት፣ ያደጉበት፣ የተማሩበት፣ በስራ ተሰማርተው የከበሩበትና ደስታ ያዩበት ሆኖ ሳለ፤ የህወሀት መሪዎች ግን፣ የአማራውን ህዝብ እንደጠላት በመቁጠር፣ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን በማዛባት፣ የቦታዎችን፣ መሪዎችንና የህዝቡን አቀማመጥ አዛብተው የሚጽፉ ሆዳሞችን እየቀጠሩ የዘር ጥላቻ በመዝራት ላይ ተሰማርተዋል። በዚህ ዓይነት ጸረ አማራ፣ ጸረ ጎንደር ዘመቻ ተባባሪ በመሆን፣ በጠለምት፣ በወልቃይት፣ በቃብቲያ፣ በሁመራና በዳንሻ ነባሩን ህዝብ የሚያፈናቅሉ የትግራይ ተወላጆች ተግባር እጅግ አሳዝኖናል።

ላለፉት 30 ዓመታት የአማራው ህዝብ በተለይም የጎንደር ህዝብ የአሳየውን ትዕግስትና አስተዋይነት፣ እንደ ፍርሀት በመቁጠር፣ ብዙ የህወሀት ድጋፍ ማህበሮች፣ በጎንደር ህዝብ ላይ የተካሄደውን ሽብር ከመደገፍ አልፈው፤ የወያኔ የሽብር ዘመቻ እንዲቀጥል ጥሪ አድርገዋል። በዚህ አጋጣሚ ለሀገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች የምናሳስበው፤ በርካታ የወልቃይት ጠገዴና አርማጭሆ ተወላጆች ደርግን በመጥላት፣ የተሻለ አስተዳደር ይመጣል በሚል ተስፋ ከህወሀት/ኢህዴን ጎን ተሰልፈው ታግለዋል፤ ብዙዎችም በባድሜ ጦርነት ተሰውተዋል። በሰለጠነው አለም የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፤ ወያኔ ከሽብር ተግባሩ እንዲቆጠብ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የቀረቡ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መጠየቅ ሲገባቸው፣ ዛሬ በ21ኛው ክፈለዘመን የአበደን መንግስት ደግፈው ያስተላለፉት መግለጫ እጅግ አሳስቦናል።

ከዚህም አልፎ፣ ከሁመራ እስከ ቋራ ባለው የድንበር አካባቢ በመንግስት ድጋፍ ኗሪውን እያፈናቀሉ የእርሻ መሬቶችን ለደጋፊዎቻቸው በማከፋፈል ዘመቻ ቀጥለዋል። ህወሀትና የፌዴራል ወኪሎቹ የአማራን ህዝብ እንደጠላት በመቁጠር፣ የኢትዮጵያን ለም መሬት ለሱዳን ሊሸጡ የሚያካሂዱትን ውል ህዝቡ እንደማይቀበለው በቁርጠኝነት መወሰኑ ይታወቃል። ከጥንት ዘመን ጀምሮ፣ የአርማጭሆ ህዝብ የሀገሩን ድንበር ለመከላከል የመንግስንት ፈቃድ አይጠይቅም። ጠላት ሲመጣ ወደ መሪዎች ፈቃድ ከመጠይቅ ይልቅ፣ ቀድመው ወራሪውን ያጠቁ ነበር። ለምሳሌ፣ በ1960ዎቹ ሱዳኖች ወደ ደንበር ጥሰው የኢትዮጵያን መሬት ለማረስ ሲሞክሩ፣ ጀግናው የአርማጭሆ ህዝብ መንግስትን ፈቃድ ሳይጠይቅ፣ በጎበዝ አለቃ አስተባባሪነት፣ በራሱ ስንቅና ትጥቅ ዘምቶ፣ ሱዳኖችን አባሮ መሬታችንን ሙሉ በሙሉ ነጻ በማድረግ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከአውለበለበ በኋላ ነው ለኢትዮጵያ መንግስት ያስታወቀው። በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ተማሪዎችና በፓርላማው የተደነቀ ተግባር ሆኖ ተነግሮለታል። በዚህ ዘመቻ፣ ሱዳኖች ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከኢትዮጵያ በኩልም እነ ገብሬ ወልደመድህን፣ ድረስ አይናለም፣ አዜ አበራና ሌሎችም ተሰውተዋል። በዚያን ጊዜ ለተሰው ጀግኖች በአስለቃሽ፤ ”የጎደቤ አሞራ ነብስህን አይማረው፣ ጥንት ገሎ ቀለበህ ዛሬ እሱን በላኸው“ ተብሎ ተገጥሞላቸው ነበር። ዛሬ ወያኔ ይህን በደማችን የተከበረ መሬታችንን ነው ለሱዳኖች ሊሸጥ የሚዋዋለው። ጀግናው የአርማጭሆ ህዝብ ግን ህወሀት ወደደም ጠላም፤ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን አይሸጥም ብሎ ወስኗል። ዛሬም እንደ ጥንቱ በደሙ ያስከብረዋል።

ይሁን እንጅ፣ ህወሀት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘምና የመስፋፋት አላማውን ለማሳካት፣ የአርማጭሆን ህዝብ ከሱዳን ወታደር ጋር እየተባበረ ህዝቡን ያስጠቃል “የሱዳንን ጭቁን ገብሬ መሬት ለመውሰድ የሚፈልጉ ትምክህተኞች“ በማለት ይከሳል። ለሱዳን ወታደር ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ ታሥረው በሱዳን ወህኒ ቤት እንዲማቅቁ ያደርጋል። ይህን የመሰለ ከሀገር መሪዎች የማይጠበቅ አስነዋሪ ተግባር ስንመለከት በእርግጥ ይህ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው ወይ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንዲሉ፣ ህወሀት የሾማቸው የፌደራል ባለስልጣኖች፤ እነ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝና ከትግራዩ ገዥዎች ከነ አቶ አባይ ወልዱ ትዕዛዝ እንደማይወጡ ግልጽ ሆኗል። ይህን የህወሀት ስርዓት የተገነዘቡ የሱዳን ባለስልጣኖችም የአማራን ህዝብ በመወንጀል ወያኔ ታማኝ ወዳጃቸው እንደሆነ ሳይደብቁ ይናገራሉ። በኛ እምነት፣ የራሱን ህዝብ ከመሬቱ እያፈናቀለ ለሌላ ሀገር የሚሸጥ መንግስት እድሜ አይኖረውም። የመቀሌው አባይ ወልዱና የአዲስ አበባው ሀይለማሪያም ደሳለኝ፣ ከሱዳን ወዳጆቻቸው ጋር በመመሳጠር፣ በአማራው ህዝብ ላይ የሚያካሂዱት የማጥላላት ዘመቻና ሥር የሰደደ ሴራ ምክንያት ብዙ ሀገር ወዳጅ ጀግኖች ከሁመራ እስከ ቋራ ባለው የኢትዮጵያ መሬት ህይወታቸውን አጥተዋል። ወያኔ ከሱዳን መንግስት፣ ከድርጅቶችና ከደርግ መንግሥት ሠርጎ በመግባት ብዙ ግድያዎችንና ሰቆቃዎችን አከናውኗል።
ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን እንዘረዝራለን፤ በ1975 ዓም የጣሊያን ዘመን እውቅ አርበኛ የነበሩት ቢትወደድ አዳነ መኮነን፣ ታጋይ አበበ ጀምበርና በርካታ ታጋዮች ከሱዳን ወደ ሀገራችን ተመልሰን እንታገል ብለው በጉዞ ላይ እንዳሉ፣ ወገን መስለው በተቀላቀሉ አሸባሪ ቡድን በርሀ ላይ ተጨፍጭፈዋል። ቢትወደድ አዳነን ያህል ሰው መግደል፣ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ መሪ ለማሳጣትና የጎንደርን ህዝብ ትግል ለማዳፈን የተጠነሰሰ ሴራ ለመሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ፣ እነ ታጋይ ሻለቃ ዋክሹም ነወጠ፣ ታጋይ ሻለቃ ዘለቀ ጀምበር፣ ታጋይ ሻለቃ በሪሁን ገብረየስ፣ ታጋይ ሻለቃ ሰፈፈ በላይ፣ ታጋይ ሻለቃ ተድላ ወልደማሪያም የመሳሰሉ እውቅ የጎንደር አርበኞች በረቀቀ የሴራ በርሀ ላይ ተጨፍጭፈዋል። የጎንደር ችግር በዚህ አላበቃም፣ ሱዳኖች የጎንደር አርበኞች በዚህ መንገድ ወደ ደንበሩ እየሄዱ ማለቃቸውን ስለሚፈልጉ፣ ሱዳን ውስጥ ያሉትንም ማንገላታት ጀመሩ።

በ1977 ዓ.ም ወያኔ ወደ ወልቃይት ጠገዴ ገብቶ ህዝቡ ማሸበርና ማፈናቀል ሲጀምር፣ ሱዳን ውስጥ የነበሩ ጎንደሬዎች ከፋኝ በሚል ስም ተደራጅተው ወያኔ በህዝቡ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ መቃወም ጀመሩ። በተለይም የወልቃይ ጠገዴና የአርማጭሆ ተወላጆች የሆኑት፤ እነ ታጋይ ሻለቃ ጌታቸው ይርጋ፣ ታጋይ ሻለቃ አስራደ በየነ፣ ሻለቃ አበጀ ፈለቀ፣ ሽለቃ መከታው አዛናውና ሌሎች በርካታ ታጋዮች ወያኔ ከሀገራችን በአስቸኳይ ይውጣ ብለው መንቀሳቀስ እንደጀመሩ በሱዳን መንግስት የስለላ ቡድንና በወያኔ ትብብር ታፍነው ተወስደው ደብዛቸው ጠፍቶ ቀርቷል። በተጨማሪ ሱዳን ውስጥ የነበሩትን የጎንደር ተወላጆች፣ በተለይም ጀኔራል ነጋ ተገኝን፣ ኮሎኔል እምሩ ወንዴና ሻለቃ አጣናው ዋሴን በቁም ስር እንዲሆኑ ተበይኖባቸው፣ ወያኔ እንደልቡ ጎንደርን እንዲቆጣጠር በሱዳን በኩል በግልጽ ተመቻቸለት።

ከዚያም፣ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ፣ ቅድሚያ ተግባሩ ያደረገው ለወዳጁ ለሱዳን መንግስት ውለታ የኢትዮጵያን መሬት አሳልፎ መስጠት ነበርና፣ ይህ አላማ ይቃወማሉ የሚላቸውን ሀገር ኢትዮጵያውያን በያሉበት ማሳደድ ጀመረ። በ1999 ዓም አካባቢ ፣ የወያኔና የሱዳን የጋራ ሀይል ያነጣጠረው በታዋቂው አርበኛ በታጋይ ሻለቃ አጣናው ዋሴ ላይ ነበር። የወያኔ መንግስት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ለመስጥት ውስጥ ለውስጥ መዋዋል ሲጀምር፣ ሱዳን ሀገር የነበሩት ታጋይ አጣናው ዋሴ፣ አርበኞችን አደራጅተው ወደ ሀገራቸው ገብተው ጦርነት ሊጀምሩ ይችላል በሚል ፍርሀት፣ ሻለቃ አጣናውን ከ15 ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሱዳን መንግስት ታፍነው ለወያኔ ተላልፈው፤ ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ በወያኔም በእስር ቤት ተሰቃይተው እንዲሞት ሆኗል። ይህን መግለጽ የፈለግነው፣ አብዛኛው ወገናችን የጎንደር ህዝብ ያሳለፈውን መከራ እንዲያውቀው ለማድረግ ነው።
በመጨረሻም፣ እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የአርማጭሆ ተወላጆች፤
1. የወያኔ የሽብር ግብረኃይል በጎንደር ህዝብ ላይ የከፈተውን ወረራና የፈጸመውን ወንጀል በጥብቅ እናወግዛለን፣
2. ጀግናው የጎንደር ህዝብ፣ ህወሀት የከፈተበትን ወረራ ለመከላከል የፈጸመውን ተጋድሎና የከፈለውን መጽዋዕትነት፣ ከልብ እየደገፍን፣ አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ከጉኑ ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናችን እናረጋግጣለን፣
3. በወያኔ የጦር ሀይል ለተገደሉ፣ ለቆሰሉና ለታሰሩ ወገኖቻችን ሁሉ ልባዊ ሀዘናችንን እየገለጽን፣ ለቤተቦቻቸውና ለሰፌው የጎንደር ህዝብ መጽናናትን እንመኛለን፤
4. በህወሀት የሽብር ግብረሀይል እየታፈኑ የታሰሩ ሰላማዊ የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ አባላት፣ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አቶ አታላይ ዛፌና ሌሎችም ወገኖቻችን በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፣ ያነሱትን ፍትሀዊና ህጋዊ የአማራ የማንነት ጥያቄ ከልብ እንደግፋለን፣
5. የጎንደር ህዝባዊ አርበኛ ከቆላና ከደጋ ተሰባስቦ፣ የጎንደርን ህዝብ ከወያኔ ጥቃት ለመከላከል የፈጸመውን ጀግንነት እያደነቅን፣ የከተማይቱ ወጣትም ከህዝባዊ አርበኛው ጎን ተሰልፎ ያሳየው ንቁ ተሳትፎ እና ወገኖቻችን አሳልፈን አንሰጥም ብሎ ያሰማው እምቢተኝነት ድምጽ እጅግ አኩርቶናል፣
6. በታች አርማጭሆ፣ አብደራፊና አብርሀጅራ ኗሪዎችን ከእርሻ ከመሬቱ እያፈናቀለ የቀድሞ ወታደሮቹን በማስፈር በነባሩ የአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ህገወጥ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆጠብና በአካባቢው የሰፈሩ ህወሀት ወታደሮች በአስቸኳ ወደ ትግራይ ጦር ሰፈራቸው እንዲመልስ እናሳስባለን።

7. በህወሀት የጦር ሀይል ከጎንደር የተወሰዱት፣ የጸለምት፣ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የሰቲት ሁመራ ወረዳዎች በአስቸኳይ ወደ ጥንት ይዞታቸው ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር እንዲመለሱ እንጠይቃለን፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የአርማጭሆ ጉዳይ ኮሚቴ armachihoguday@gmail.com

No comments:

Post a Comment