(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 30/2011) የዘንድሮው የቡና ቱሪዝም ቀንን ለማክበር የወጡት መግለጫዎች አይወክሉኝም ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ዓለም ዓቀፍ የቡና ፕሮግራም በቡና መገኛ ምድር በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል አስመልክቶ በሳምንቱ መጀመሪያ በተሰራጨው መግለጪያ የቡና መገኛ ጂማ ነው የሚለው አገላለጽ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዛሬ እንዳስታወቀው ከመስሪያ ቤቱ ዕውቅናና ተልዕኮ ውጪ የተሰራጨው መግለጫ በማስተባበል ችግሩን የፈጠረውን አካል አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
በካፋ ቦንጋ ለሶስተኛ ቀን ተቃውሞ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ላይ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን ዝግጅት ላይ መሆናቸው ከተገለጸ ወዲህ በያዝነው ሳምንት የተሰራጨው መግለጫ ከፍተኛ ውዝግብ ከመፍጠር ባለፈ ህዝባዊ ተቃውሞ ቀስቅሷል።
የውዝግቡ መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር እያዘጋጀ ያለው የቡና ቱሪዝም ቀን ቀድሞ በታቀበትና የቡና መገኛ ተብሎ በተጠቀሰው የካፋ ዞን የሚከበር እንደሆነ የሚገልጸው መረጃ ተቀይሮ በጅማ እንደሚከበር መገለጹ ነው።
ጅማ የቡና መገኛ መሆኗን በመጥቀስ የተቀየረውና የበዓሉን የማክበሪያ ቦታ የሚገልጸው መግለጫ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ መውጣቱን ተከትሎ ቁጣ ሊቀሰቀስ ችሏል።
የካፋ ዞን አስተዳደር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ በመጻፍ የእርምት ርምጃ እንዲሰጥበት በይፋ የጠየቀ ሲሆን በቦንጋ ከተማ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ በማሰማት ላይ ይገኛል።
ለሶስተኛ ቀን በቀጠለው የቦንጋ ተቃውሞ መንገዶች ተዘግተው፣ እንቅስቃሴዎች ተገድበው ውለዋል።
ቅሬታ የቀረበበት የመንግስት አካል የሆነው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተነሳውን ውዝግብ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፌስ ቡክ ገጽ ባሰራጨው ጽሁፍ ጉዳዩን አስተባብሎታል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህዳር ወር መጨረሻ የሚከበረውን የቡና ቱሪዝም ቀን ከ400 በላይ የውጭና በሺዎች የሚቆጠሩ የሃገር ውስጥ ተሳታፊዎች በሚገኙበት በአፍሪካ ህበረት የስብሰባ ማዕከል በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ሰሞኑን የተሰራጨው መግለጫ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ተልዕኮና አቋም የማያንጸባርቅና የተዛባ መረጃ ነው ብሎታል።
የቡና ቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ ከቡና ምርትና የአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ የግንዛቤ መድረክ ለማስተዋወቅ በፌስቡክ እና በድረ-ገጽ አድራሻዎች እንዲሁም በሚኒስቴሩ መገናኛ ዘዴዎች እየሰራን ባለንበት ሂደት ከቡና መገኛ አካባቢ ጋር በተያያዘ የባለስልጣኑ ተልዕኮና አቋም ያልሆኑና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መልዕክቶች በተለያዩ ቀናት መተላለፋቸውን ተገንዝበናል ያለው የባለስልጠን መስሪያ ቤቱ የተሰራጨው መረጃ የመንግስት አቋም ያለመሆኑን እየገለጽን ችግሩን የፈጠረውን አካል አጣርተን ርምጃ እንወስዳለን ብሏል።
ለተፈጠረው የመረጃ መዛባትም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይቅርታ ጠይቋል።
No comments:
Post a Comment