(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 6/2011) በሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር አዛዥና በኢጋድ የዋና ጸሃፊው የፖለቲካ አማካሪ ኮለኔል ገብረእግዚአብሔር አለምሰገድ በተለምዶ ገብሬ ዲላ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
በኮንትሮባንድ ንግድና በሶማሌ ክልል በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩት ኮለኔል ገብረእግዚያብሄር ባለፈው ሳምንት በጂጂጋ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በመሪነት እንደተሳተፉ ይነገራል።
ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ለ10 ተከታታይ አመታት የቆዩት ኮለኔል ገብረእግዚያብሄር በሃገር ሃብት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ካደረሱ የህውሃት የጦር መሪዎች ዋናው እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ በ1999 ዓ.ም በሶማሊያ የእስላማዊ ፍርድ ቤት የተሰኘውን ቡድን ለመውጋት በሚል ሰበብ ባልተጠና እና በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዞ 43ኛ ክፍለ ጦርን እየመሩ ወደ ሶማሊያ እንዲገባ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲያልቁ ያደረጉ በሚል የሚወነጀሉ ናቸው።
ክፍለ ጦሩም እንዲደመሰስ በማድረግ ሰራዊቱን በትኖ በመሸሽ የራሳቸውን ህይወት ብቻ ያተረፉ እንደሆነም ይታወቃል።
ኮለኔል ገብረእግዚያብሄር በመሳሪያ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለሶማሊያ የተለያዩ የጦር አበጋዞች መሳሪያ በመሸጥ ከፍተኛ ሀብት ማካበታቸውም ይነገራል።
በተለምዶ ጄነራል ገብሬ ዲላ በሚል የሚታወቁት ኮለኔል ገብረእግዚያብሄር የሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይቆም ሚና ተጫውተዋል ተብለው በሶማሊያውያን ዘንድ የሚወቀሱ እንደሆኑም ይታወቃል።
በቅርቡ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ለኢሳት እንደገለጹት ኮለኔል ገብረእግዚያብሄርና ጄነራል አብረሃም ወልደምርያም በጅጅጋ ለተፈጠረውና የሰው ህይወት ላጠፋው ግጭት በቀጥታ እጃቸው አለበት።
እነዚህ ግለሰቦች ከቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ጋር በመሆን ከሶማሌላንድ እስከ ደቡብ ሱዳን የተዘረጋ የኮንትሮባንድ ንግድ ሲመሩ እንደነበረ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በዚህ የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ ኔትወርክ በመፍጠር እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በጥፋት መስመር ላይ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
ኮለኔል ገብረእግዚያብሄር አለምሰገድ በቁጥጥር ሲውሉ ከእሳቸው ጋር የነበሩትና የቀድሞ የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ጄነራል አብርሃም ወልደማያም ወይም ኳርተር ግን ሸሽተው መቀሌ መግባታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment