(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011) በአፋር የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ሲደረግ ዋለ።
አሳይታ፣ አዳአር፣ በራሂሌ፣ ገላኢሉ፣ ዳሎል፣ ገዋኔና ኮነባ በተሰኙ የአፋር ከተሞች በተደረገው ተቃውሞ የክልሉን መንግስት የሚመራው ገዢ ፓርቲ ለህዝብ ስልጣኑን እንዲያስረክብ ተጠይቋል።
ሁለተኛ ወሩን እያጠናቀቀ ያለው የአፋር ተቃውሞ ፌደራል መንግስቱ በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ የክልሉ ህዝብ ከተደቀነበት አደጋ እንዲታደገው ጥሪ ቀርቧል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ ለኢሳት እንደገለጸው የፌደራሉ መንግስት በቶሎ ምላሽ ካልሰጠ በአፋር ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል ተቃውሞ ይቀሰቀሳል።
በህወሃት የሚደገፈው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝቡን ጥያቄ ወደጎን በማድረግ አፈናና እስር በመፈጸም ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል ተቃውሞ እየቀረበባቸው ያሉት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም አወል ስልጣኔን እለቃለሁ ማለታቸው ተሰምቷል።
አፋሮች ዛሬ አደባባይ ወጥተዋል። በስድስት ከተሞች የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ ጥያቄዎቹ ተመሳሳይ ናቸው።
የህወሃት ረጅም እጆች ከአፋር ላይ ይነሱ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የለውጥ ሂደት አፋር ላይ በአስቸኳይ ይጀመር፣ የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር ስልጣኑን ይልቀቅና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ይዘው የወጡት አፋሮች ፌደራል መንግስቱ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ የተጠናከረ ተቃውሞ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ዛሬ በአሳይታ ዳሎል ገዋኔ አዳአር በራሂሌ ገላኢሉና ኮነባ ከተሞች የተደረጉት የተቃውሞ ትዕይንቶች የአፋር ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል የሚል መልዕክት በስፋት እንዲሰማ ተደርጓል።
በተለይ በአሳይታ ተቃውሞ ለሁለተኛ ጊዜ በማድረግ የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር ስልጣኑን እንዲያስረክብ ተጠይቋል።
የህወሃት ጣልቃ ገብነትና ለረጅም ዓመታት በስልጣን የቆዩ የክልሉ አመራሮች ከስልጣናቸው ይውረዱልን፣ አዲስ የተማረ ሃይል ቦታውን ይረከብ የሚሉ መፈክሮች በስድስቱ ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተንጸባርቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረጉ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር ልዩ ሃይል በወሰደው ርምጃ በርካታ ወጣቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከ20 በላይ ሰዎች መታሰራቸው መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ ለፌደራል መንግስት ባስተላለፈው መልዕክት በሙሰኛ አመራሮች የእርስ በእርስ የሃይል ግጭት የአፋር ህዝብ ዋጋ መክፈል የለበትም ብሏል።
የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ለኢሳት እንደገለጹት የአፋር ህዝብ ትዕግስቱ እየተሟጠጠ በመሆኑ የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ መፍትሄ ካልሰጠው ሁኔታዎች የከፉ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜናም ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እየደረሰባቸው የሚገኙት የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ስልጣኔን እለቃለሁ ማለታቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንቱ አቶ ስዩም አወል ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል።
በተደጋጋሚ ስልጣን እለቃለሁ የሚሉት ፕሬዝዳንቱ የፓርቲ ሊቀመንበርነቱን ቦታ ለቤተሰባቸው አባል ለመስጠት ማቀዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የክልሉን የስልጣን ቦታ እንደንጉስ መዋቅር ለቤተሰብ እንዲተላለፍ አቅደዋል የተባሉት አቶ ስዩም የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ካልገባ በክልሉ ያለውን የሰላም አደጋ ሊያባብሱት እንደሚችሉ ከወዲሁ እየተገለጸ ነው።
የህወሃት አገዛዝ ቀጥተኛ ድጋፍ ያላቸው አቶ ስዩም እስከመጨረሻው ድረስ እንዲታገሉና ካልሆነም መቀሌ መጥተው እንዲቀመጡ በህወሃት በኩል ዋስትና እንደተሰጣቸው የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል
No comments:
Post a Comment