Monday, November 19, 2018

ጠበቃ ለማቆም ገንዘብ የለኝም በማለት በችሎት ፊት ምለው የተናገሩት አቶ ኢሳያስ ዳኘው (የሜ/ጀነራል ክንፈ ወንድም) ሚሊዬነር መሆናቸው ተረጋገጠ!

BBC Amharic

ከዚህ ቀደም በራሳቸው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ለተናገሩት አቶ ኢሳያስ ዳኘው ፖሊስ አለኝ ያለውን ማስረጃም አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል። በራሳቸው ስም በፀረ ሙስና ኮሚሽን የሐብት መዝገብ ቅፅ ላይ ራሳቸው ያስመዘገቡት ዝርዝር
➤ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ባለ 1 ፎቅ ቤት በራሳቸው ስም የተመዘገበ፣

➤ በባለቤታቸው ስም የተመዘገበ 6 ክፍል ያለው ቤት፣
➤ 115 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የጋራ ሕንጻ፣
➤ 240ሺህ ብር የሚያወጣ ቶዮታ ኮሮላ፣
➤ ግምቱ 1 ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ የሆነ ሎደር፣
➤ የአንበሳ ባንክ ባለድርሻ፣ በንግድ ባንክ፣
➤  በዳሸንና በአዋሽ ባንክ በርካታ ገንዘብ መቆጠባቸውን ማረጋገጡን ፖሊስ ተናግሯል።

ፖሊስ ግለሰቡ ከሀገር ሊሸሹ ሲሉ አየር መንገድ ላይ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ጠቅሷል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ሀብቱ የተመዘገበው በ2003 ዓ.ም መሆኑን ጠቅሶ አሁን ሀብቱ ለሌላ ተላልፎ ወይም ተሽጦ መሆን አለመሆኑን በተጨባጭ ስለማያሳይ የተከላካይ ጠበቃው አገልግሎት መቀጠል አለበት ሲል ተከራክሯል።

ባለቤታቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑና ሎደሩም የባለቤታቸው ነው በማለትም አስረድቷል። ፖሊስ በበኩሉ ሀብቱ በ2003 ቢመዘገብም በየሁለት ዓመቱ ሀብቱ መኖር አለመኖሩን የማሳወቅ ወይም የማደስ ኃላፊነት ነበረባቸው፤ ይህንን ካላደረጉ ንብረቱ እንዳለ ነው የሚቆጠረው በማለት ተከራክሯል። በተጨማሪም የባልና ሚስት ሐብት የጋራ ሀብት ነው ይህንንም ራሳቸው መዝገብ ያሰፈሩት በፈቃዳቸው ነው ሲል አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በቂ ሀብት ስላላቸው ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ያቆመላቸው ጠበቃ ተነስቶ በራሳቸው ጠበቃ በማቆም እንዲከራከሩ ውሳኔ አስተላልፏል። ፖሊስም በፍርድ ቤቱ ፊት በሀሰት ምለው የግል ጠበቃ ለማቆም ገንዘብ የለኝም በማለታቸው አስተማሪ ቅጣት እንዲጣልባቸውም ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጫማሪ የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል።

No comments:

Post a Comment