(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 22/2011)የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ድብደባ ለመፈጸም ሙከራ በማድረጋቸው በህግ ሊጠየቁ ነው ተባለ።
ዶክተር አሸብር የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሁለት አባላትን በስብሰባ ላይ ለመደብደብ መሞከራቸው ተገልጿል።
በዶክተር አሸብር የድብደባ ሙከራ ከተደረገባቸው አንዷ ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ መሆኗም ታውቋል።
ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሊያመራ መሆኑን የገለጹት ምንጮች በዶክተር አሸብር በኩል የሽምግልና ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሰዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ለድብደባ የሚያደርስ ጉዳይ አልተፈጠረም በማለት አስተባብለዋል።
ትላንት ጠዋት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ ነበረው። የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስና የኮሚቴ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ እየተለዋወጡ ነበር።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ስብሰባው እየተካሄደ እያለ በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስና የኮሚቴው ዋና ጸሃፊ በሆኑት በወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ መካከል የሀሳብ ልዩነት ይከሰታል።
ልዩነቱ ይከርና በዶክተር አሸብር በኩል ሃይለቃል መወርወር ይጀመራል።
በስብሰባው የነበሩ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኮሚቴ አባል እንደሚሉት ዶክተር አሸብር ግልጽ የሆነ ዘለፋ በወይዘሮ ዳግማዊት ላይ ይሰነዝራሉ።
በዚህን ጊዜ የኮሚቴ አባል የሆነችው ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ ጣልቃ ትገባና ዶክተር አሸብርን ትቃወማለች።
በዚህ ጊዜ ነበር ዶክተር አሸብር ለድብደባ የተጋበዙት።
የኢሳት ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት እኔ የወሰንኩትን ማክበር ሲገባቸው ለምን ይቃወሙኛል በማለት በሁለቱ የኮሚቴ አባላት ላይ የድብደባ ሙከራ አድርገው በስብሰባው ላይ በነበሩ ሰዎች ገላጋይነት ሊበርድ ችሏል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በስብሰባው ላይ የተፈጸመውን የሃሳብ ልዩነት መካረር አምነው ለድብደባ ግን አልተጋበዝኩም ብለዋል። ምንም የተፈጠረ ነገር የለምም ሲሉ አስተባብለዋል።
ምንም እንኳን ዶክተር አሸብር ስለትላንቱ በኮሚቴው አባላት ላይ የሞከሩት ድብደባ ሀሰት ነው ቢሉም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዳያመራ ኮለኔል ደራርቱና ወ/ሮ ዳግማዊት ዘንድ ሽማግሌ መላካቸው ታውቋል።
የሽምግልናው መጨረሻ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ዶክተር አሽብርን በህግ ለመጠየቅ ሁለቱ ግለሰቦች እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ኢሳት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉንና ወይዘሮ ዳግማዊትን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
No comments:
Post a Comment