(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 22/2011)በጋምቤላ የቦምብ ጥቃት ደረሰ።
በአንድ የክልሉ ባለስልጣን ጠባቂ ፖሊስ ትላንት የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የሁለት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱ ተገልጿል።
አዲሱ የጋምቤላ አመራር ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ያኮረፉ ሃይሎች የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለም ታውቋል።
ቦምቡን ያፈነዳው ግለሰብ የህወሃት አባል እንደሆነም የኢሳት ምንጮች ያደረሱን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተደረገው የጋምቤላ ገዢ ፓርቲ ግምገማ የክልሉ ፕሬዝዳንትና ምክትላቸው በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።
ትላንት ምሽት በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ያፈነዳውን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አራት ቆስለዋል።
የክልሉ አንድ ባለስልጣን ጠባቂ እንደሆነ የተነገረለት ይህው ግለሰብ የቦምብ ጥቃቱን ለምን እንደፈጸመ የታወቀ ነገር የለም።
ጥቃቱን የፈጸመው ጠባቂ አብሮት ከነበረ ባልደረባው ጋር ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በአቅራቢያ ካሉ ሰዎች አራቱ መለስተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።
እንደምንጮች መረጃ ከሆነ የባለስልጣኑ ጠባቂ የህወሃት አባል ነው።
ባለፈው ሳምንት በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን የለቀቀው የጋትሉዋክ ቱት አመራር በህወሃት ሰዎች የተከበበ እንደሆነ ይታወቃል።
የህወሃት አባላት የጋምቤላ ምክርቤት አባል እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ የባለስልጣናቱ አብዛኞቹ ሹፌሮችና ጠባቂዎች የህወሃት አባላት ናቸው።
የጋምቤላ ክልል በኢኮኖሚና በፖለቲካ የህወሃትን ጥቅም እንዲያስከብሩ ቁልፍ ቦታዎችን የሚቆጣጠሩት ህወሃቶች መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
የጋምቤላ የእርሻ መሬትን ከ70 በመቶ በላይ የተቆጣጠሩት የህወሃት አባላት የሆኑ ባለሀብቶች እንደሆኑ በዓለምዓቀፍ ተቋማት ሪፖርት ጭምር የተጋለጠ እንደነበር ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር በጋምቤላ እንቅፋት እንዲገጥመውና የለውጥ ሂደቱ ጋምቤላ እንዳይጀመር በህወሃት ቁጥጥር ስር የነበረው የጋትሉዋክ ቱት አመራር መሰናክሎች ሲፈጥር መቆየቱ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የጋምቤላ ገዢ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአዲስ አበባ ግምገማ ባደረጉ ጊዜ ክልሉን በህወሀት ዘመን የጭቆና አመራር እንዲቀጥል ያደረጉትን ፕሬዝዳንቱንና ምክትላቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን እንዲለቁ መደረጋቸው ለህወሃት አገዛዝ መልካም ዜና አልሆነም።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የጋምቤላው ገዢ ፓርቲ ግምገማ በአዲስ አበባ እንዲሆን የተደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ከተጽዕኖ ውጪ ሆነው እንዲወስኑ ነው።
ህወሃት በአዲሱ የጋምቤላ አመራር ደስተኛ ባለመሆኑ በክልሉ የሰላም መደፍረስ ሊከሰት እንደሚችል ከወዲሁ ስጋቱ እየተገለጸ ነው።
የትላንቱ የቦምብ ጥቃትም የህወሃት አባል በሆነ የጋምቤላ ክልል ባለስልጣን ጠባቂ መፈጸሙ ከአዲሱ አመራር መምጣት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
No comments:
Post a Comment