Sunday, February 25, 2018

“እኔ ተፈታሁ እንጂ፤ የታሰርኩበት ዓላማ አልተፈታም” ኢየሩሳሌም ተስፋው

የሐበሻ ወግ፡- ኢየሩሳሌም ተስፋው፤ በቅድሚያ በቅድሚያ ከእስር ስለተፈታሽ እንኳን ደስ አለሽ?

ኢየሩሳሌም፡- ለወጉ ያህል “እንኳን ደስ አለህ” ልበልህ እንጂ፤ እኔ እንኳን ብዙም ደስ አላለኝም፡፡


የሐበሻ ወግ፡- ማለት?

ኢየሩሳሌም፡- ገና ነው፤ ደስታችን ሙሉ አይደለም፡፡

የሐበሻ ወግ፡- መልካም፤ አንቺም የተከሰስሽውና የታሰርሽው በግንቦት ሰባት የተነሳ ነው….



ኢየሩሳሌም፡- አዎ፤ ከ2005 ዓ.ም  ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በሰላማዊ ትግል ስሳተፍ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ተደብድቤአለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ መንግስት በሰላማዊ ትግል ይለወጣል ብዬ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ እናም ከእኔ ጋር አብረው ከተከሰሱት ልጆች ጋር ብዙ ተመካከርን፡፡ ከረዥም ጊዜ ምክክር በኋላ ያለን አማራጭ ሁለት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን፡፡ አገር ጥሎ መሰደድ ወይም የትግል አማራጭ መቀየር፡፡ ሀገር ጥሎ መውጣት ወይም መሰደድ በእኛ እምነት ተመራጭ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የትግል አማራጭ መቀየርን ነበር ምርጫ ያደረግነው፡፡ በዚህ ውሣኔአችን መሰረት የግንቦት ሰባትን ትግል ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ስንሄድ ነው መንገድ ላይ የተያዝነው፡፡ 

የሐበሻ ወግ፡-  ይቅርታ ላቋርጥሽ፤ አሁን ዕድሜሽ ስንት ነው?

ኢየሩሳሌም፡- ሃያ ስድስት፡፡

የሐበሻ ወግ፡- እስር ቤት ስንት ዓመት ቆየሽ?

ኢየሩሳሌም፡- ሶስት ዓመት፡፡ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ከገባሁ ደግሞ 5 ዓመት ሞላኝ፡፡

የሐበሻ ወግ፡- በ20ዎቹ እድሜ መጀመሪያ ማለትም በ23 ዓመት ዕድሜሽ የትጥቅ ትግል ውስጥ ለመግባት መወሰን ከባድ ይመስለኛል …..

ኢየሩሳሌም፡- ከባድ ነው፡፡ ግን ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በሰላማዊ ትግል ስሳተፍ የነበሩት ሂደቶች፣ የደረሱብን በደሎችና ግፎች ካለ ዕድሜዬ እድሜዬ እንድበስል ያደረጉኝ ይመስለኛል፡፡ እና እንዳልከው እዚህ ውሣኔ ላይ (በተለይም ሴት ሆነህ) መድረስ ከባድ ነው፡፡ በተለይ በዚያ ወቅት ስለ ግንቦት ሰባት ማሰብ በራሱ በጣም ያስፈራ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰላማዊ ትግሉ በር ስለተዘጋ በውሣኔአችን መፅናት ነበረብን፡፡ 

የሐበሻ ወግ፡- አስታውሳለሁ፤ ፍ/ቤትም በቀረብሽ ጊዜ “የሰላማዊ ትግል በር ስለተዘጋ ነው በትጥቅ ትግል መሣተፍን አምኜበት ነው ወደ ኤርትራ ያመራሁት” ነው ያልሽው ….

ኢየሩሳሌም፡- አዎ፤ እኔም ጓደኞቼም ማይካድራ ላይ ከተያዝንበት ቅፅበት ጀምሮ ይህንኑ ነው ፊት ለፊት የነገርናቸው፡፡

የሐበሻ ወግ፡- እስቲ ወደ ኤርትራ ስትሄዱ በቁጥጥር ስር እስከዋላችሁበት ጊዜ በመንገድ ላይ የነበረውን/የገጠማችሁን ውጣ ውረድ አውጊኝ? 

ኢየሩሳሌም፡- የተነሳነው ከዚህ ከአዲስ አበባ ነው፡፡ ያን ዕለት ባህርዳር ገብተን አደርን፡፡ በበነጋታው ከመሃላችን አንዱ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ የቀረነው ወደ ጎንደር ጉዞ ቀጠልን፡፡ … እናም ጎንደር ገባን፡፡ ከዚህ በኋላ የነበረው ጉዞአችን አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሙቀቱ፣ ውጣውረዱ ወ.ዘ.ተ ሁሉ እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ በተለይ ለእኔ ከቤቷ ወጥታ ርቃ ሄዳ ለማታውቅ ወጣት ጉዞው ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ፡፡ በነገራችን ላይ ከጎንደር በኋላ ፍፁም መንቀሳቀስ በማንችልበት ደረጃ ክትትል ይደረገብን እንደነበርና እንደምንያዝም እናውቅ ነበር፡፡ ቢሆንም ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ ማይካድራ ላይ ተያዝን፡፡ 

የሐበሻ ወግ፡- ከተያዛችሁ በኋላስ ምን ሆነ? ምን ገጠማችሁ?

ኢየሩሳሌም፡- ከተያዝን በኋላ ለረዥም ሰዓት በቪዲዮ ቀረፁን፡፡ ከዚያም ዐይናችንን አስረው በመኪና ወሰዱንና አንድ ቤት ውስጥ አስገቡን፡፡ ዐይናችን ስለታሰረ ያ ቦታ የት እንደሆነ አላወቅንም፡፡ ብቻ እዚያ ቤት ውስጥ ሶስት ቀን ካሳደሩን በኋላ እንደገና ዐይናችንን አስረው ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱን፡፡ ስገምት፤ ይኼኛው ቦታ ጎንደር ይመስለኛል፡፡ እዚያም አራት ቀን ከቆየን በኋላ ነው ወደ ማዕከላዊ ያመጡን፡፡ ማዕከላዊ መሆኑን ያወቅነው ከመኪና ከመውረዳችን በፊት መዓት ፖሊሶች ከበባ ሊያደርጉብን ሲጯጯሁ በሰማነው ድምፅ ብዛትና ትርምስ ነው፡፡

የሐበሻ ወግ፡- አዲስ አበባ ማዕከላዊ ግቢ ከደረሳችሁ በኋላ ከበባ?

ኢየሩሳሌም፡- አዎ፤ ስንያዝ ጀምሮ የነበረው ሁኔታ በጣም ያስቅ ነበር፡፡ (ሣቅ) በአየር ወለድ ጭምር ታጅበን ነበር ወደ ከቦታ ቦታ የምንወሰደው፡፡ እኛ ሶስት ወጣቶች ነን፤ በዚያ ላይ በእጃችን ምንም ነገር እንዳልያዝን ይታወቃል፡፡ መንግስት እኛን ለማጀብ ከፖሊስ በተጨማሪ አየር ወለድ ጭምር ማሰለፉ በጣም ያሳዝናል፤ ያስቃል፡፡

የሐበሻ ወግ፡- በአየር ወለድ ጭምር መታጀባችሁን በምን አወቅሽ?

ኢየሩሳሌም፡- ስገምት ጎንደር ሊሆን ይችላል ብዬ የነበርኩህ ቦታ ለቀናቶች ቆይተናል፡፡ አጃቢዎቻችን (ጠባቂዎቻችን) በሙሉ መሣሪያ ታጥቀዋል፡፡ አንዱ አጃቢያችን ግን መሣሪያ አልያዘም ነበር፡፡ እናም “ሁሉም መሣሪያ ታጥቀዋል፤ አንተ ግን መሣሪያ አልያዝክም፤ ለምንድነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ያኔ ወገቡ ላይ ያለውን ገመድ አሳየኝ፡፡ “ይኼ መሣሪያ ነው እንዴ?” ስለው፤ “አዎ” አለኝ፡፡ ገረመኝ፡፡ ያ ሁሉ ፌዴራል ፖሊስ መሣሪያ ወድሮብን ነው እየተጠበቅን ያለው፡፡ ለእኛ በጥፊ ለምንወድቅ ምንም ነገር ላልያዝን ወጣቶች አየር ወለድ ማሰለፍ ለምን እንዳስፈለገ አላውቅም፡፡

የሐበሻ ወግ፡- በነገራችን ላይ፤ እንዲህ ዓይነት ውሣኔ ላይ መድረስሽን ጉዞ መጀመርሽን ለአንድ ሰው፣ በጣም፣ እጅግ በጣም ለምትቀርቢው ሰው እንኳ አልነገርሽም?

ኢየሩሳሌም፡- በፍፁም! እንዴት ይነገራል!? ቅድም እንዳልኩህ ውሣኔአችን እጅግ ከባድ ነው፡፡ ሲጀመር፤ የትጥቅ ትግል የኔ ምርጫ አልነበረም፡፡ ደም አፍስሶ፣ ህይወት ቀጥፎ ለውጥ ማምጣትን አላምንበትም፤ ጓደኞቼም አያምኑበትም፡፡ በመንግስት እርምጃ ተገደን ነው እዚህ ውሣኔ ላይ የደረስነው፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ ነበረብንና እዚህ ውሣኔ ላይ መድረሴን ለማንም ትንፍሽ አላልኩም፡፡

የሐበሻ ወግ፡- አሁን ከእስር ቤት ወጥተሽ “ሰፊውን እስር ቤት” ተቀላቅለሻል፡፡ ከወጣሽ በኋላ ያለውን ሁኔታ አየሽው?

ኢየሩሳሌም፡- አሁን በውጪ ያለው ነገር ጥሩ ይመስላል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ለ2 ዓመታት በሰላማዋ ትግል ተሳትፌአለሁ፡፡ ያኔ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻልንም ነበር፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ገና ከፓርቲው ግቢ ወጣ ስንል ነበር ታፍነን፣ ስንደበደብና ስንታሰር ማንም ዞር ብሎ አያየንም ነበር፡፡ አሁን ግን ሕዝቡ ዳር እስከዳር ተንቀሳቅሷል፡፡ በሕዝቡ አመፅ እጃቸው ተጠምዝዞ ሳይወዱ በግዳቸው የፖለቲካ እስረኞችን እንዲለቁ አስገድዷል፡፡ ይኼ የሕዝብ አንድነት መንፈስ ጥሩ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ቦታዎች የሚከሰቱ ሁኔታዎች አሁንም ሕወሐት/ኢህአዴግ በከፈተልን መንገድ እየፈሰሰ ያለ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ የዘረኝነት አዝማሚያ ጫፍ እየነካ ያለ ይመስለኛል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ከተለያየ ክልል የመጣን እስረኞች ነን አንድ ላይ የነበርነው፡፡ ከሱማሌ፣ ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ወ.ዘ.ተ፡፡ ሁላችንንንም የፖለቲካ እስረኞች አንድ የሚያደርገን ነገር ነበር፡፡ እርግጥ ነው ሁላችንም የምንታገለት ዓላማ አለን በመሃላችን የሃሳብ ልዩነት አለ፤ ግን…..የጋራ የሚባል አገር የሚባል ነገር አንድ ያደርገን ነበር፡፡ ከእስር ቤት ውጪ ግን የዘረኝነት አስተሳሰብ እየገነነ ያለ ይመስለኛል፡፡ ዘረኝነት የሚባለውን ነገር ከመሃላችን ካላስወጣን የምንፈልገው የሥርዓት ለውጥ ቢመጣ እንኳን ዋጋ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በአንድነት ጠንክረን መውጣት አለብን፡፡

የሐበሻ ወግ፡- መልካም፤ ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ትቀጥያለሽ ?

ኢየሩሳሌም፡- አዎ እቀጥላለሁ፡፡ ጥያቄዬ እኮ ገና አልተመለሰም፡፡ እኔ ተፈታሁ እንጂ፤ የታሰርኩበት ዓላማ አልተፈታም፡፡ ስለዚህ በትግሌ እቀጥላለሁ፡፡

የሐበሻ ወግ፡- ስለነበረን አጭር አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment