አቅመ ደካሞች ለሆኑት በየወሩ ቋሚ ክፍያ በመስጠት እንዲሁም ሌሎቹን ደግሞ በአካባቢ ጽዳትና መሰል ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ገንዘቡ እንደሚከፈላቸው ተመልክቷል። በፍጹም ድህነት ውስጥ ከሚገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች 32ሺ የሚሆኑት አቅመ ደካሞች በመሆናቸው በነፍስ ወከፍ በወር 170 ብር በቤተሰብ ቁጥር ተባዝቶ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል። ቀሪዎቹ 168ሺ የሚሆኑት ደግሞ የአካባቢ ልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የአለም ባንክ ክፍያውን እንደሚፈጽም መረዳት ተችሏል። የአለም ባንክ በፍጹም ድህነት ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመደበው 450 ሚሊየን ዶላር 70 በመቶው ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መመደቡን የከተማ አስተዳደሩን ሃላፊ ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል። በአዲስ አበባ ከተማ በ55 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 200ሺ ያህል ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ይህ የእርዳታ ፕሮግራም ለአስር አመታት እንደሚቀጥልም ተመልክቷል። የአለም ባንክ በፍጹም ድህነት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት በ2009 የጀመረው ይህ ፕሮጀክት እስከ 2018 እንደሚቆይም ከዘገባው መረዳት ተችሏል። ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከሚገኙ ሀገራት በድህነት ከአለም ከመጨረሻ ሁለተኛ መሆኗን አለምአቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ። ከኢትዮጵያ በታች የመጨረሻ ድሃ ተብላ የምትጠቀሰው ወይንም ኢትዮጵያ የምትበልጣት ብቸኛ ሀገር ኒጀር መሆኗም ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment