ኢሳት (ጥር 30 ፥ 2009)
በአፋር ክልል ልዩ ስሙ ዞን ሶስት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ስፍራው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከቀናት በፊት በሁለት አርብቶ አደሮች ላይ የፈጸሙት ግድያ በአካባቢው ውጥረት መቀስቀሱ ተገለጸ።
በዚሁ አካባቢ ወልጅ አልባ የሰፍሩ ወደ ስድስት ሺ አካባቢ ተቀናሽ ወታደሮች ከአርብቶ አደሮች ጋር አለመግባባት ውስጥ በመሆናቸው ተደጋጋሚ ግጭቶች በመከሰት ላይ መሆናቸውን የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሃላፊ የሆኑት አቶ ጋአስ አህመድ ለኢሳት አስታውቀዋል።
በዚሁ ስፍራ የሚገኙት ተቀናሽ ወታደሮች በአንድ አርብቶ አደር ላይ የፈጸሙት ድብደባ አለመግባባትን ቀስቅሶ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከፈቱት ተኩስ ሁለቱ ሊሞቱ መቻላቸውን ሃላፊው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
አርብቶ አደሮቹ ድብደባ የፈጸሙበት ግለሰብን እና እናሳክመዋለን ስጡን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ የተኩስ እርምጃ በመውሰድ ሁለቱ አርብቶ አደሮችን እንደገደሉ አቶ ገሃስ የሟቾቹን ስም በመጥቀስ ድርጊቱን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ በወሰዱት በዚሁ እርምጃ፣ የአንደኛው ህይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፣ ሁለተኛው አርብቶ አደር ግን ለህክምና በመወሰድ ላይ እንዳለ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።
የግጭቱ መከሰት ተከትሎም በአሁኑ ወቅት አካባቢው በውጥረት ውስጥ መሆኑን የተናገሩት የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሃላፊ አርብቶ አደሮቹ በተለያዩ ጊዜያት የሚደርሱባቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን በመግለጽ ላይ መሆናቸውንም አክለው አስታውቀዋል።
በቅርቡ በአካባቢው እንዲሰፍሩ የተደረጉ ተቀናሽ ወታደሮች ከአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ጋር አለመግባባት ውስጥ በመሆናቸው መንግስት ለጥበቃ በሚል በርካታ የሰራዊት አባላት በስፍራው ማሰማራቱን አቶ ጋሃስ አህመድ አስረድተዋል።
ክልሉን ከትግራይ ክልል ጋር በሚያዋስኑ ሶስት ወረዳዎች አዲስ አለመግባባት መኖሩን የገለጹት ሃላፊው በቅርቡ በዚሁ ስፍራ የአንድ የትግራይ ክልል ነዋሪ ህይወት ማለፉን ውጥረት መቀስቀሱ ተናግረዋል።
የግለሰቡ ገዳይ ተላልፎ ይሰጠን ያሉ የትግራይ ክልል ተወካዮች በአሁኑ ወቅት መጋሌ ተብሎ በሚጠራ የአፋር ክልል በርካታ ሚሊሺያዎችን አስፍረው እንደሚገኙ የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት አክሎ አስታውቀዋል።
በአፋር ክልል የሚገኙ አርብቶ አደሮች የክልሉ መንግስት እያደረሰብን ነው ላሉት ችግር ዝምታን በመምረጡ ምክንያት ራሳችንን መከላከል አለብን ወደ ሚል እርምጃ እየገቡ መሆኑን የድርጅቱ ሃላፊ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በአካባቢው ስላለው አለመግባባትም ሆነ ስለሁለቱ አርብቶ አደሮች ግድያ የአፋር ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም።
በቅርቡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል ከሶማሊ ክልል ጋር በሚያዋስነው ስፍራ ግጭት ተቀስቅሶ ቁጥሩ ያልተገለጸ ሰው ህይወት ማለፉን መንግስት መግለጹ የሚታወስ ነው። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በበኩሉ ዕርምጃው በሶማሊና በፌዴራል መንግስት ድጋፍ በሚደረግላቸው የመንግስት ታጣቂዎች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለ ድርጊት መሆኑን ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment