ኢሳት (ጥር 29 ፥ 2009)
የኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንበት ድንበር በቅርቡ ለሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው ግጭት የመንግስት አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገለጸ።
የኦሮሚያ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በፌዴራልና በሶማሌ ክልል አስተዳደር ድጋፍ የሚደረግላቸው የመንግስት ታጣቂዎች በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ ግድያና ዘረፋን እየፈጸሙ ናቸው ሲል ባለፈው ሳምንት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በአካባቢው በመንግስት ታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ዕርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወቀው ፓርቲው ድርጊቱ የኦሮሚያ ክልል ይዞታን በሃይል ለመውሰድ የታለመ እንደነበርም አመልክቷል።
በዚሁ የሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች እየተካሄደ ስላለው ግጭት ምላሽን የሰጡ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የመንግስት ሃላፌዎች በግጭቱ ሚና አላቸው ሲል በኦፌኮ የተሰጠውን መረጃ አረጋግጧል።
ይሁንና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የመንግስት አካላት በግጭቱ መሳተፋቸውን ይፋ ቢያደርጉም በአመራሮቹ ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ይኑር አይኑር የሰጡት መረጃ የለም።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በግጭቱ የሚሳተፉ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ በሳምንቱ መገባደጃ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት በግጭቱ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውንም ቢያረጋግጥም ቁጥሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።
በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ወረዳዎች ተቀስቅሶ ያለውን ግጭት ዕልባት ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ አዲሱ አክለው ገልጸዋል።
በሁለቱ ክልሎች ተቀስቅሶ የነበረን የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ በ1997 አም ህዝበ ውሳኔ ተካሄዶ እንደነበር ያወሱት ሃላፊው የአስተዳደር ወሰን ማካለል ያልተደረገባቸው ቀበሌዎች የማካለል ስራ እንደሚካሄድባቸው ይፋ አድርገዋል።
በ1997 አም ተካሄዷል በተባለው ህዝበ ውሳኔ ሁሉም ወረዳዎች በምን ምክንያት የሚካለል ስራ እንዳልተከነወነባቸው የክልሉ መንግስት የተሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ አዲስ የሚካሄደውም የክልል ማዋሰን ዕርምጃ መቼ እንደሚጀምር የታወቀ ነገር የለም።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በፌዴራልና በሶማሌ ክልል የመንግስት ታጣቂዎች እየተፈጸመ ነው ያለው ግድያና ዝርፊያ አዲስ ስጋት ማሳደሩን ይገልጻል።
No comments:
Post a Comment