ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የተከሰተው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች በጊዚያዊ መጠለያ እንዲሰባሰቡ በመደረግ ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ አስታወቀ።
የአርብቶ አደሮችን ህይወት ለመታደግ ሲባል እየተወሰደ ባለው በዚሁ ዘመቻ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማትና መንግስት ለተጎጂዎቹ የምግብ አቅርቦት እንደሚያደርጉ ድርጅቱ ገልጿል።
ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ በተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጣቸው ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአፋርና፣ የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በድርቁ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የተመድ መረጃ ያመለክታል።
በሶማሌ ክልል እየደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚገልጸው ድርጅቱ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርቁን ለመታደግ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል።
በኦሮሚያ ክልል በቦረናና ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሞ እና በአብዛኛው የሶማሊ ክልል የቤት እንስስሳት በድርቁ ሳቢያ እየሞቱ መሆናቸው ተመድ አስታውቋል።
ይህንኑ የድርቅ አደጋ ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ችግሩ እስከተያዘው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ድረስ ቀጣይ እንደሚሆን ተተንብዮአል።
መንግስት በበኩሉ የድርቁን አደጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍን እንዲሰጥ ጠይቋል።
በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ህጻናት በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ ሁኔታ በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳይገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ በድጋሚ መከስቱ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የእርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment