ኢሳት (ጥር 29 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን የቤት ችግር ይቀርፋሉ ተብለው ግንባታቸው የተጀመረ የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጄክቶች የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠማቸው ተገለጸ።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኮንትራክተሮችና እቃ አቅራቢዎች ለሰሩት ስራ ክፍያ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ችግር ውስጥ እንደሚገኙና ስራቸውንም ማከናወን የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን እንዳስታወቁ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ እትሙ ዘግቧል።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ግንባታ ላይ የተፈጠረው መስተጓጎል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አሰራር በመጀመሩ ምክንያት ነው ሲል ምላሽን ሰጥቷል።
የስራ ተቋራጮች ለፈጸሙት ግንባታና ለተቀሩ ስራዎች ማስኬጃ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው ክፍል ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክፍያ መፈጸም ማቆሙ ተመልክቷል።
በዚሁ ችግር የተነሳ በርካታ ሰራተኞች ደሞዝ እየተከፈላቸው እንዳልሆነና የግንባታ ሂደቱም መስስተጓጎሉን ለመረዳት ተችሏል።
የከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከሶስት አመት በፊት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መዝግብው እንደነበር ይታወሳል።
እነዚሁ ነዋሪዎች ቤቶችን ለማግኘት በመንግስታዊ ባንኮች ቁጠባን ሲያካሄዱ የነበረ ሲሆን ቤት ፈላጊዎች የቤቶቹ ግንባታ መስተጓጎል ስጋት እንዳሳደረባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ከ2006 አም ጀምሮ በ40/60 ፕሮግራም ግንባታቸው የተጀመሩ ከ37 ሺ በላይ ቤቶች ግንባታቸው በአማካይ በ10 በመቶ ውስጥ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
በርካታ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መንግስት አጋጥሞት ያለው የፋይናንስ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የሃገሪቱ የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና የእዳ መጠን እየበዛ መምጣት ለተፈጠረው የፋይናንስ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ሆነው የተቀመጡ ሲሆን፣ የአለም ባንክ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲያደርግ ሲያሳስብ ቆይቷል።
No comments:
Post a Comment