ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ የቱርክ መንግስት የሽብርተኛ ድርጅት ነው ሲል ከፈረጀው የጉለን ንቅናቄ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ትምህርት ቤቶችን ለቱርክ አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑ ተቃውሞን አስነሳ።
ባለፈው ሳምንት በቱርክ ጉብኝትን ያደረጉ ፕሬዚደንት (ዶ/ር) ሙላቱ ተሾመ መንግስታቸው በኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶችን ለቱርክ መንግስት ለማስተላለፍ መወሰኑ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና ነጃሺ ኢትዮ-ቱርኪሽ ኢንተርናሽናል በመባል የሚጠሩትት አምስት ትምህርት ቤቶች መስራች የሆኑ ሃላፊዎች ተቋማቸው በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የተቋቋመና ዕውቀና ተሰጥቶት የአገሪቱን ህግጋት አክብቶ የሚሰራ የትምህርት ተቋም እንጂ አሸባሪ አይደለም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
በድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሌሊል አይዲን ትምህርት ቤታቸው ከቱርክ ተቋማትና ከቱርክ መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አስታውቀዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት በቱርክ ጉብኝታቸው እነዚሁ ትምህርት ቤቶች የቱርክ መንግስት ላቋቋመው ማሪፍ የትምህርት ፋውንዴሽን ተላልፈው ይሰጣሉ ባሉት ጉዳይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ሃላፊው ገልጸዋል።
ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የግል ሃብታችንን ኢንቨስት አድርገን ትምህርት ቤቶቹን መስርተናል የሚሉት አይዲን እና አጋሮቻቸው የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ንክኪ እንደሌላቸውና የቱርክ መንግስት የጉለን አሸባሪ ቡድን ከሚላቸው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው አክለው አስረድተዋል።
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ጉብኝትን ያደረጉ የቱርክ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በነጋሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ተላልፈው ለመንግስት እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ በወቅቱ ምላሽን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ትምህርት ቤቶቹ ህግን እና የመማር ማስተማር ሂደትን በማይጎዳ መልኩ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ መግለጻቸውን የቱርኩ የዜና አውታር አናዱሉ ዘግቧል።
የትምህርት ቤቶቹ ህልውና ጥያቄን ባስነሳበት ወቅት ባለፈው ሳምንት በቱርክ ጉብኝትን ያደረጉት ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ መንግስታቸው ትምህርት ቤቶቹን አሳልፎ እንደሚሰጥ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የቱርክ መገኛኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው አይዘነጋም።
እርምጃው በከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ማረጋገጫ ማግኘቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶቹን እንዲያቋቋሙ በመግለጽ ላይ ያሉ የቱርክ ባለሃብቶች ስጋት እንዳደረባቸው ከሃገሪ ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ የነጃሺ ኢትዮ-ቱርኪሽ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ስር አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመቀሌና አለም ገና ከተሞች አምስት ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከትምህርት ቤቱ ድረ-ገጽ ለመረዳት ተችሏል።
በትምህርት ቤቶቹ ከጀማሪ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ 2ሺ አካባቢ የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment