ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)
የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና አርሲ ዞን ብቻ በ20 ቀናት ውስጥ 240 ሰዎች መገደላቸውን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ ገለጸ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ከመስከረም 28/2009 እስከ ጥቅምት 18/2009 በአርሲ ነገሌ ብቻ 70 ሰዎች ሲገደሉ፣ 335 መታሰራቸውን የገለጸው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ፣ ከዚህ በተጨማሪም በሻላ እና አጄ በተባሉ አካባቢዎች 85 ሰዎች ሲገደሉ 400 የሚሆኑት ደግሞ መታሰራቸውን ገልጿል።
የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በላከው በዚሁ ባለ ዘጠኝ ገፅ ሪፖርት በኦሮሞዎች በይበልጥም በወጣቶች ላይ የተነጣጠረው ጥቃት እኤአ ከ2005 ጀምሮ ላለፉት ለ12 አመታት ተጠናክሮ መቀጠሉን ዘርዝሯል።